'ድረገጽ' ምንድን ነው?

እስቲ አማርኛን የማሰልጠን መዋጮአችንን 'website'ን በአማርኛ ቃል/ሃረግ በመተካት ሙከራ እንጀምረው።

በኮምፒውተሮች መካከል መረጃ የሚተላለፍበትን የግንኝት ትብታብ (internet) ብዙውን ጊዜ በአማርኛ 'የመረጃ መረብ' ሲባል እንሰማለን። ይህ የስያሜ ሃረግ ከእንግሊዝኛው ጥምር ቃል መሰረቱን 'net'ን 'መረብ' ብሎ የመረቡን መረጃ መተላለፊያነት በማገናዘብ የተደራጀ ነው። ከዚያም እንግሊዝኛው 'መረብ'ን በ'ድር' እየተካ 'worldwide web', 'website', 'webpage' ሲል በአማርኛ ኋለኞቹ በአንድነት 'ድረገጽ' ተብለዋል።

በ'site' እና በ 'page' መካከል ያለው ልዩነት ጕልህ ነው። ‘website’ን ‘ድረገጽ’ ከልማድ የተነሳ ይወክለው እንደሆን እንጂ አይገልጸውም። ገላጭ ስያሜ ለመስጠት 'worldwide web'ን 'አለምአቀፍ የመረጃ ድር' እንበለው። ይህን የግንኝቱ ትብታብ የፈጠረውን ድር፣ መረጃ አስተላላፊዎች እየተመሩ እንደሚሰፍሩበት እና እንደሚያቀኑት ሰፊ ቦታ ብናየው፣ 'website' ማለት አንድ የመረጃ ስርጭት አገልግሎት ሰጪ ከዚህ ሰፊ ቦታ የሚያገኘው አንድ ምሪት ወይም ቅኝ ነው። ይህ ቅኝ ቋሚ ርስትነት የሌለው ጊዜያዊ የአገልግሎት መስጫ ቦታ ነው። ስለዚህ የመገናኛ ትብታብነቱን (ድርነቱን) ለማመልከት ከላይ ያየነውን 'የመረጃ መረብ’ የሚለውን ሃረግ ይዘን ለምሪትነቱ (ቅኝነቱ) ደግሞ የአገልግሎት መስጫነቱን እንዲያመለክት ‘ጣቢያ’ን ወይም ‘ትኩል’ን ጨምረን 'የመረጃ መረብ ጣቢያ' ወይም ‘የመረጃ መረብ ትኩል’ ብንለውስ?

'ጣቢያ' ከ'አጥቢያ' (በዙሪያው ያሉትን መንደሮች የሚያገለግል ቤተክርስቲያን) የሚዘመድ 'የአገልግሎት ማእከል' የሚል ፍች ሊሰጠው የሚችል ከ'station' ጋር የሚተካከል ቃል ነው። 'ትኩል'ም 'ተከለ' ከሚለው ስርወቃል የሚፈጠር ከእንግሊዝኛው 'post' ጋር የሚተካከል ፍች የያዘ ቃል ነው። ሃረጉ ረዝሞ ቢገኝ በምሕጻረ ቃል መወከሉ ወይም ሃሳቡን ጠቅልሎ ሊወክል የሚችል አጭር ቃል ቢገኝ በሱ መተካቱ ኋላ ይሆናል።