አበይት ነገሮች

ሰይ ብል!

በየማኅበራዊ መገናኛዎችና በሌሎችም የአስተያየት መስጫ ‘ድረገጾች’ ላይ ‘like’ እና ‘unlike’ ደምበኛ የአስተያየት ህዝበኝነት (ተወዳጅነት) መመዘኛ ቃላት ሆነዋል። እነዚህ ቃላት እንዳሉ ወደአማርኛ ገብተው “እባካችሁ ይህን ድረገጽ፣ አስተያየት፣ ወዘተ. ላይክ አድርጉት” እየተባለ ሲጻፍ እናያለን። መተቸቱን ትተን በመፍትሔው ላይ ለማተኮር፣ በአማርኛ ‘like’ን ምን እንበል ስንል በቶሎ የሚመጣልን ቃል ‘ወደደ’ ነው። ግን “እባካችሁ ይህን ... ውደዱት” ማለትን ውስጣችን የሚቀበለው አይመስልም። ለዚህ አንዱ ምክንያት እንደማንኛውም አዲስ ነገር ቃሉን በአዲስ አገባብ መልመዱ ጊዜ ከመሻቱ የተነሳ ቢሆንም፣ አቢዩ ምክንያት ግን በእንግሊዝኛው በ‘like’ እና ‘love’ የሚገለጹትን ገርና ምር የፈቃደ ልቡና ስሜቶች ጠቅልሎ የያዘ የዘወትር ቃል በመሆኑና ይህን ብቸኛ ቃል ከእንግሊዝኛው አንጻር ለሌላ ሶስተኛ አገባብ ማላመዱ ፍቹን ስለሚያደበዝዘው ነው።

አማርኛ እኮ ሌላ ተመሳሳይ ስርወቃል አለው፤ እሱም ‘ሰየ’ ይባላል። ከብዙው በጥቂቱ የተለመዱት ውልድ ቃላቱ የሚከተሉት ናቸው፦ “(አ)ሻ”፣ “እሰይ”፣ “እሺ”። “ተሰየ”ን የአማርኛ መዛግብተቃላት እንደሚከተለው ይፈቱታል፦ “ጐመዠ፣ ተቃረ፣ ጓጓ፣ ቋመጠ” (ደስታ ተክለወልድ)፣ “ጎመዠ መብልንም ኾነ መጠጥን ወይም ውብ መልከ መልካም ሴትን ዐይቶ በዐሳቡ በልቡ ተመኘ ጎመጀ ሰየ” https://dictionary.abyssinica.com/። የመዛግብተ ቃላቱ አፈታት የሚያመለክተን ቢያንስ ከዛሬ ግማሽ ምእት አመት በፊት ገደማ የነበረውን የቃሉን አገልግሎት ነው። ከተለመዱት ውልድ ቃላቱ የምናገኘው ስሜት ግን ልክ እንደእንግሊዝኛው ‘like’ በገሩ የሚገለጽ ምኞትና የልቡና ፈቃድ ነው። እስቲ ገባ ብለን የውልድ ቃላቱን ስሜት እንመርምር።

“የቃላት ትንታኔና ፈጠራ” በሚል ርእስ ባቀረብኩት ቀዳሚ ጽሑፍ እንዳመለከትኩት [ሸ] በ [ይ] የቀለመ [ሰ] መሆኑን ይዘን ስንነሳ ‘አሻ’ እና ‘እሺ’ በውስጣቸው ‘ሰየ’ን መያዛቸውን ለመቀበል አያዳግተንም። አሻኝ “አሰየኝ (አሰኘኝ)፣ ፈቀድኩ ተመኘሁ”፣ እሺ ደግሞ “እሰይ፣ ፈቀድኩ፣ ይሁን አልኩ” ማለት ነው። የተመኘነው ወይም የምንፈቅደው ነገር ሲሆን የሁልጊዜ የደስታ ስሜት መግለጫችን በቀጥታ “እሰይ[አለሁ]” ነው።

እኔ ለጨዋታ በደረስኩበት ዘመን የብይ ጨዋታ በአዲስ አበባና ምናልባትም በሌሎች ትላልቅ ከተሞች የወንዶች ልጆች ተወዳጅ ጨዋታ ነበር። በዚያ ዘመን የነበራችሁ እንደምታስታውሱት በጨዋታው መሃል “ሰይ ብል/ባትል” የሚል የባለተራና የሌሎች ተፎካካሪዎች እሽቅድድም ነበር። ወደአጨዋወቱ ህግ ዝርዝር ሳንገባ፣ ባለተራ የሆነ ተጫዋች ለራሱ ብይ ይቀርባል ወይም ለመምታት ይቀናኛል ያለውን አንድ የተፎካካሪ ብይ አመልክቶ እሷኑ ብቻ ለመምታት ማለም አለበት። ነገር ግን በታላሚው ብይ አጠገብ ወይም በማስፈንጠሪያው አግጣጫ ሌሎች ብዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከብዙዎች መሃል መምታት ይቀልላልና ሌሎች ተፎካካሪዎች ሳያግዱት ቀድሞ “በኢላማዬ አግጣጫ ካሉት ብዮች የመታሁት እንደኢላማ ይቆጠርልኝ” ለማለት “ሰይ ብል” ይላል፤ “ያለምኩለት ባይሆንም የመታሁትን ብወድድ” ማለት ነው። እንግዲህ “ሰየ” “የሆነውን ነገር ፈቀደ፣ ይሁን አለ፣ ወደደ” ማለት ከሆነ “ሰይ አለ” ለእንግሊዝኛው “ላይክ” ጥሩ ምትክ ይሆናል እላለሁ። በዚሁ አንጻር ደግሞ “አይ” ማለት ነገርን ያለመውደድ፣  ያለመቀበል መግለጫ ስለሆነ ለ“ሰይታ” ተቃራኒ ወይም “ሰይታ”ን ለመሰረዝ በ”አንላይክ” ምትክ “አይ አለ” “አይታ” ይሆናል። የነዚህን ቃላት አገባብ በተግባር ለማየት በአማርኛ የመረጃ መረብ ጣቢያ (ድረጉልት) የ‘ውይይት’ አምድን ጎብኙ፤ በአስተያየትም ተሳተፉ፤ “ሰይ” ብዬ ሰድጄ አንከረባብቼ እንደሆነ ንገሩኝ። እንግዲህ ‘ላይክ/አንላይክ ማድረግ’ ይቅር፤ “ሰይታ”ና “አይታ”ንም ተላመዷቸው።

| pdf | አስተያየት

'ድረገጽ' ምንድን ነው?

እስቲ አማርኛን የማሰልጠን መዋጮአችንን 'website'ን በአማርኛ ቃል/ሃረግ በመተካት ሙከራ እንጀምረው።

በኮምፒውተሮች መካከል መረጃ የሚተላለፍበትን የግንኝት ትብታብ (internet) ብዙውን ጊዜ በአማርኛ 'የመረጃ መረብ' ሲባል እንሰማለን። ይህ የስያሜ ሃረግ ከእንግሊዝኛው ጥምር ቃል መሰረቱን 'net'ን 'መረብ' ብሎ የመረቡን መረጃ መተላለፊያነት በማገናዘብ የተደራጀ ነው። ከዚያም እንግሊዝኛው 'መረብ'ን በ'ድር' እየተካ 'worldwide web', 'website', 'webpage' ሲል በአማርኛ ኋለኞቹ በአንድነት 'ድረገጽ' ተብለዋል።

በ'site' እና በ 'page' መካከል ያለው ልዩነት ጕልህ ነው። ‘website’ን ‘ድረገጽ’ ከልማድ የተነሳ ይወክለው እንደሆን እንጂ አይገልጸውም። ገላጭ ስያሜ ለመስጠት 'worldwide web'ን 'አለምአቀፍ የመረጃ ድር' እንበለው። ይህን የግንኝቱ ትብታብ የፈጠረውን ድር፣ መረጃ አስተላላፊዎች እየተመሩ እንደሚሰፍሩበት እና እንደሚያቀኑት ሰፊ ቦታ ብናየው፣ 'website' ማለት አንድ የመረጃ ስርጭት አገልግሎት ሰጪ ከዚህ ሰፊ ቦታ የሚያገኘው አንድ ምሪት ወይም ቅኝ ነው። ይህ ቅኝ ቋሚ ርስትነት የሌለው ጊዜያዊ የአገልግሎት መስጫ ቦታ ነው። ስለዚህ የመገናኛ ትብታብነቱን (ድርነቱን) ለማመልከት ከላይ ያየነውን 'የመረጃ መረብ’ የሚለውን ሃረግ ይዘን ለምሪትነቱ (ቅኝነቱ) ደግሞ የአገልግሎት መስጫነቱን እንዲያመለክት ‘ጣቢያ’ን ወይም ‘ትኩል’ን ጨምረን 'የመረጃ መረብ ጣቢያ' ወይም ‘የመረጃ መረብ ትኩል’ ብንለውስ?

'ጣቢያ' ከ'አጥቢያ' (በዙሪያው ያሉትን መንደሮች የሚያገለግል ቤተክርስቲያን) የሚዘመድ 'የአገልግሎት ማእከል' የሚል ፍች ሊሰጠው የሚችል ከ'station' ጋር የሚተካከል ቃል ነው። 'ትኩል'ም 'ተከለ' ከሚለው ስርወቃል የሚፈጠር ከእንግሊዝኛው 'post' ጋር የሚተካከል ፍች የያዘ ቃል ነው። ሃረጉ ረዝሞ ቢገኝ በምሕጻረ ቃል መወከሉ ወይም ሃሳቡን ጠቅልሎ ሊወክል የሚችል አጭር ቃል ቢገኝ በሱ መተካቱ ኋላ ይሆናል።

| pdf | አስተያየት

አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን! [ክፍል ሁለት] የቃላት ትንታኔና ፈጠራ በአማርኛ

“አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን!” በሚል ርእስ ባቀረብኩት የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፍ በታቀደ ልማት ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር እውቀትን የልማት ሃይል ማድረግ፤ እውቀትን ለመቀበል፣ ለመፍጠርና ለማስፋፋት ቋንቋን ማዘመንና ማሰልጠን፤ ቋንቋን ለማዘመንና ለማሰልጠን ደግሞ ውስጣዊ ስርአቱን ከመገንዘብ ተነስቶ የእውቀትና የዘመናዊ አስተሳሰብ መግለጫ የሚሆኑ አዳዲስ ቃላትን እያበጁ የፈጠራ አቅሙን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አመልክቼ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ አዳዲስ የአማርኛ ቃላትን ወደመፍጠር የሚመራ የቃላት ፍች ትንታኔ ዘዴ በምሳሌ አሳያለሁ ባልኩት መሰረት እነሆ ይህን ተከታይ ጽሑፍ አቅርቤአለሁ።

አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን! በሚል ርእስ ባቀረብኩት የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፍ በታቀደ ልማት ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር እውቀትን የልማት ሃይል ማድረግ፤ እውቀትን ለመቀበል፣ ለመፍጠርና ለማስፋፋት ቋንቋን ማዘመንና ማሰልጠን፤ ቋንቋን ለማዘመንና ለማሰልጠን ደግሞ ውስጣዊ ስርአቱን ከመገንዘብ ተነስቶ የእውቀትና የዘመናዊ አስተሳሰብ መግለጫ የሚሆኑ አዳዲስ ቃላትን እያበጁ የፈጠራ አቅሙን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አመልክቼ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ አዳዲስ የአማርኛ ቃላትን ወደመፍጠር የሚመራ የቃላት ፍች ትንታኔ ዘዴ በምሳሌ አሳያለሁ ባልኩት መሰረት እነሆ ይህን ተከታይ ጽሑፍ አቅርቤአለሁ።

በቅድሚያ ለትንታኔው መነሻ የምናደርጋቸው ስነድምጻዊ (phonological) እና ስነምእላዳዊ (morphological) ጥቅልል ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

  1. በስርወቃላት (roots) ውስጥ አቋም ያላቸው ድምጾች ተናባቢዎች (consonants) ናቸው።
  2. የቀሩት ለተናባቢዎቹ ቀለም/ዜማ ሰጪና አቋም የለሽ ዋለል (vocalic) ድምጾች ናቸው።
  3. በፍች-ተድምጽ ትንታኔ የስርወቃላትን መሰረታዊ ፍች የሚወስኑት ቅሉ (unique) ተናባቢዎች ብቻ ናቸው።
  4. ደጋሚ ተናባቢዎችን ጨምሮ የሌሎቹ ዋለል ድምጾች ተግባር ዘረቃላትን ደጕሞና አጐላምሶ ወደ ስርወቃልነት ማሳደግ ነው።
  5. በልማዳዊው የፊደል ገበታ ከሳድስ ተራ ውጭ የሚገኙ ተናባቢዎች በሙሉ የዋለል ድምጾችን ቀለም የያዙ ናቸው። ዋለል ድምጾችን በአቋም ባናገኛቸውም እንደሚከተለው አርቅቀን ልንለያቸው እንችላለን፦
  • ሳድስ (ቀለም የለሽ) ፈልቃቂ (epenthetic) ድምጽ ነው።
  • ግእዝ (ቀለም የለሽ) አናባቢ (vowel) ድምጽ ነው።
  • ካእብ ቀለመ-ው ፈልቃቂ ድምጽ ነው።
  • ሣልስ ቀለመ-ይ ፈልቃቂ ድምጽ ነው።
  • ራብዕ ቀለመ-አ አናባቢ ድምጽ ነው።
  • ሃምስ ቀለመ-ይ አናባቢ ድምጽ ነው።
  • ሳብዕ ቀለመ-ው አናባቢ ድምጽ ነው።
  1. ከተናባቢዎች መሃል እንደ [ች፣ጅ፣ሽ፣ዥ፣ጭ፣ኝ፣ይ] ያሉ ልንቅ (palatalized) ድምጾች ላንቃዊነትን የቀለሙ የድድ ወይም የትናጋ ተናባቢዎች ናቸው። ስለዚህ ከቅሉ ተናባቢዎች አይደመሩም። አቀላለማቸውም እንደሚከተለው ነው፦
  • {ች← [ት]፣ ች← [ክ]}
  • {ጅ← [ድ]፣ ጅ← [ግ]}
  • {ሽ← [ስ]፣ ሽ← [ህ]}
  • {ዥ← [ዝ]፣ ዥ← [ግ]}
  • {ጭ← [ጥ]፣ ጭ← [ቅ]}
  • ኝ← [ን]
  • ይ← [ል]
  1. “እ” እና “ህ” ጕልህ የመሰረታዊ ፍች ልዩነት የሌላቸው ተወራራሽ የጕረሮ ድምጾች ናቸው። ስለዚህ በአንድ ድምጽነት ይወከላሉ።
  2. “ው” በአቋም ሲገኝ ቅሉ ተናባቢ ነው።
  3. “ጽ” እና “ጥ” ተወራራሽ ድምጾች ስለሆኑ በ“ጠ” ይወከላሉ።
  4. [ጵ፣ፕ፣ቭ] ጨርሶ የአማርኛ መሰረታዊ ድምጾች አይደሉም።
  5. ቅሉ ተናባቢዎች የሚከተሉት ናቸው፦ [{ህ፣እ}፣ል፣ም፣ር፣ስ፣ቅ፣ብ፣ት፣ን፣ክ፣ው፣ዝ፣ድ፣ግ፣ጥ፣ፍ]
  6. በመካነ ፍጥረት ወይም በአነባበብ በሚመሳሰሉ ቅሉ ተናባቢዎች መካከልም አልፎ አልፎ ተወራራሽነትና የመሰረታዊ ፍች መቀራረብ ይታያል።

[ህ←ክ]፣ [ል←ር]፣ [ል←ን]፣ [ም←ብ]፣ [ም←ው]፣ [ም←ን]፣ [ር←ድ]፣ [ስ←ዝ]፣ [ቅ←ክ]፣ [ቅ←ግ]፣ [ብ←ፍ]፣ [ብ←ው]፣ [ት←ጥ]፣ [ክ←ግ]፣ [ው←ግ]፣ [ይ←ው]

  1. በተናባቢዎች መጥበቅና መላላት ምክንያት ፍቻቸው አሻሚ የሚሆኑ ቃላትን ለመለየት ጠባቂ ተናባቢዎችን እንደሚከተለው እንደግማቸዋለን፦ “አጋደለ” ~ “አግጋደለ”።

በልማዳዊው የስነምእላድ አስተሳሰብ ድምጾች ፍች መወከል የሚጀምሩት ተቀናጅተው ምእላድ (morpheme/ ስርወቃል) ሲሆኑ ነው። ማለትም አንድ ስርወቃል በውስጡ የተሰደሩ ድምጾች እንጂ ፍቻዊ የሆኑ ንኡሳን አሃዶች አይኖሩትም። በሌላ አባባል፣ ድምጾች ለሚመሰርቱት ስርወቃል በተናጥልም ሆነ በቅንጅት የፍች አስተዋጽኦ አያደርጉም። እንግዲህ ስርወቃላት በያዟቸው ድምጾችና በሚወክሏቸው ፍቻዊ ስሜቶች የቱንም ያህል ቢመሳሰሉ ምስስሉ ድንገተኛ ነው እንጂ ስርአታዊ አይደለም ማለት ነው።

ይህን አስተሳሰብ በምሳሌ ለማስረዳት፦ ‘ቅ’፣ ‘ል’፣ ‘ጥ’ እና ‘ፍ’ ተቀናጅተው በቀላሉ የመተጣጠፍን፣ የመዟዟርን እና የፍጥነትን ሃሳብ የሚወክል [ቅልጥፍ] የሚል ስርወቃል ይሰራሉ። ስርወቃሉም ‘ቀለጠፈ’፣ ‘ቀልጣፋ’፣ ‘ቅልጥፍና’፣ ወዘተ. የመሳሰሉትን ቃላት ለመገንባት መሰረት ይሆናል። እነዚህን ድምጾች አንድ-ለሶስት፣ ሁለት-ለሁለት ወይም ሶስት-ለአንድ እያደራጀን ብናያቸው [ቅ-ልጥፍ]፣ [ቅል-ጥፍ] እና [ቅልጥ-ፍ] ይሆናሉ። [ልጥፍ]፣ [ቅል]፣ [ጥፍ] እና [ቅልጥ] ደግሞ በየራሳቸው ስርወቃላት የሚሆኑ ቅንጅቶች ናቸው። ሆኖም አንድ ስርወቃል በውስጡ ሌላ ስርወቃል አይዝምና እነዚህ የድምጽ ቅንጅቶች በ[ቅልጥፍ] ውስጥ ያሉ ስርወቃላት ናቸው አንልም። “ድምጾች ፍች የሚይዙት ተቀናጅተው ምእላድ ሲሆኑ ነው” በሚለው አመለካከት ግን እነዚህ ቅንጅቶች ሌላ አይነት የፍች-ተድምጽ ቅንጅት ይዘውም ቢሆን የ[ቅልጥፍ] ውስጣዊ ድርጅት አሃድ ሊሆኑ አይችሉም፤ አራቱ ድምጾች በአንድነት [ቅልጥፍ]ን እስከሚፈጥሩ ድረስ ‘ቅ’ እና ‘ል’፣ ‘ል’ እና ‘ጥ’ ወይም ‘ጥ’ እና ‘ፍ’ ፍቻዊ ቅንጅት አይኖራቸውም።

በሌላ በኩል ደግሞ በ[ቅልጥፍ]ና በንኡሳኑ ስርወቃላት መካከል መብራራት የሚሻ ረቂቅ የፍች ግንኙነት ይታያል። [ቅል]ን በሚይዙ ሌሎች ስርወቃላትና ውልድ ቃላት ሁሉ የመጥጠምዘዝ፣ የመዞርና የመልለወጥ ረቂቅ ሃሳብ አለ። (መቅላት፣መቀለስ፣ መቀልመም፣ መቀልበስ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።) እንዲሁም [ጥፍ]ን በሚይዙ ስርወቃላትና ውልድ ቃላት ሁሉ የገጾች መላተምና የመጋጠም ረቂቅ ሃሳብ አለ። (ማጠፍ፣ መለጠፍ፣ ማንጠፍ፣ መዘንጠፍ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።) ከላይ የገለጽነው የ[ቅልጥፍ] ረቂቅ ፍችም የነዚህን ንኡሳን አሃዶች ፍች ያካተተ ነው። [ቅል]፣ [ቅልጥ] እና [ቅልጥፍ] [ቅል]ን ስለሚጋሩ፣ እንዲሁም [ጥፍ]፣ [ልጥፍ] እና [ቅልጥፍ] [ጥፍ]ን ስለሚጋሩ ድንገተኛ ያልሆነ የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ አላቸው። ስለዚህ ከልማዳዊው አስተሳሰብ በተቃራኒ [ቅልጥፍ] በውስጡ ፍቻዊ አሃዶችን ይዞ ይታያል።

በተለይ ደግሞ በውስጣቸው ጥንድ ተናባቢዎችን ይዘው እነዚያኑ ተናባቢዎች በከፊል ወይም በሙሉ በመድገም ብቻ የሚለያዩ ስርወቃላት የፍች ዘራቸውን ከጥንዶቹ ተናባቢዎች እንዳገኙ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ከዚህ በታች በቀረበው ሰንጠረዥ በንኡስ ተራ (ሀ) ስር በሚገኙት ስርወቃላት እንደምናየው ደጋሚዎቹ ስርወቃላት የመሰረታዊውን ጥንድ ጽንሰሃሳብ ከማራዘም፣ ከማስፋፋትና ከማጠናከር በቀር አዲስ ጽንሰሃሳብ አይወክሉም። እንግዲህ ባለብዙ ተናባቢ ስርወቃላት አነስተኛ ፍቻዊ አሃዶችን ይዘው መገኘታቸው፣ ምእላድን የፍቻዊነት መነሻ አድርገን መቍጠራችንን እንድንተው ያስገድደናል። የፍች-ተድምጽ ቅንጅቶችንም በጥልቀት ለመመርመር ከልማድ ወጥተን ንፍቅ-ምእላዳዊ (sub-morphemic) ትንታኔ ማድረግ ያስፈልገናል ማለት ነው። በንፍቅ-ምእላዳዊ አመለካከት በባለብዙ ተናባቢ ስርወቃላት ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ፍቻዊ አሃዶችን ከስርወቃላት ለመለየት ዘረቃላት (etymons) እንላቸዋለን። ዘረቃላት ቃላትን ለመገንባት ፍቻዊና ድምጻዊ መሰረቶች ናቸው። የቃላት ግንባታው አካሄድም እንደሚከተለው ይሆናል፦

ዘረቃል (+ ደጓሚዎች) = ስርወቃል → (መልከ)አምድ       = አምደቃል (+ ምእላድ) = ሙሉ ቃል

[ቅል]     + [ስ]        = [ቅልስ]   → ደራግ-1ግእዝ22ራብእ3    = ቀላስ       + ሳልስ    = ቀላሽ 

የትንታኔው አካሄድ ደግሞ የግንባታው ሂደት የኋሊት ሆኖ፣ በቅድሚያ ከሙሉቃሉ ላይ ስነምእላዳዊ ቅጥያዎችን አራግፎ አምደቃሉን መለየት፣ ከዚያም ለስርወቃሉ የአምድ መልክ የሚሰጡትን ዋለሎችንና ደጋሚ ተናባቢዎችን ትቶ የስርወቃሉን መሰረታዊ ተናባቢዎች መለየት፣ ስርወቃሉ ደጓሚዎች (ደጋሚ ተናባቢዎች፣ ውሁዳን ዋለሎች ወይም አጎላማሽ ቅጥያዎች) ካሉት እነሱን ትቶ ቅሉ ተናባቢዎችን በሰልፋቸው መለየት። የስርወቃሉን ተናባቢዎች በጥንድ የሚጋሩና በፍችም የሚቀራረቡ በቁጥር ከአራት የማያንሱ ሌሎች ስርወቃላት ካሉ ጥንዶቹን ተናባቢዎች በዘረቃልነት መወሰንና በመጨረሻም ዘረቃሉን በሚጋሩ ስርወቃላት የፍች ተመሳሳይነት ላይ ተመርኵዞ ለዘረቃሉ ፍች ማርቀቅ ነው። በሚከተለው ሰንጠረዥ እያንዳንዱን የአማርኛ ተናባቢ በአንድ ባለጥንድ ተናባቢ ዘረቃል እየወከልን በቅድሚያ በ(ሀ) ተራ ዘረቃላቱ አዲስ ተናባቢ ሳይጨምሩ በዋለሎችና በደጋሚ ተናባቢዎች እየተደጎሙ አንድ የፍች መሰረት ያላቸው የተለያዩ ስርወቃላትን እንደሚፈጥሩ እናያለን። በስርወቃላቱ የፍች አንድነት ላይ ተመስርተን የዘረቃላቱን ፍች ካረቀቅን በኋላ በ(ለ) ተራ ደግሞ ያው ዘረቃል በሌሎች ተናባቢዎች እየተደጎመ የሚፈጥራቸው የተለያዩ ስርወቃላት መሰረታዊውን ፍች እንዴት እንደሚወርሱ እናያለን። ከዚያም በፍች-ተድምጽ ትንታኔው ሊተኮሩባቸው የሚገባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለማመልከት በጥቂት ተጨማሪ ምሳሌዎች ማብራሪያ እናክላለን።

ተራ ቍጥርዘረቃልስርወቃላት በግስ መልከአምድየጋራ ፍችየጋራ ፍች በእንግሊዝኛ

1ሀ

ልግ

 

 

ላገ፣ ለገገ፣ ለገለገ

መርዘም፣ መቅጠን፣ መልለጠጥ፣ መስሳብ፣ መቀጠል

stretch, extend

1ለ

ለገ

ለገጠ/ለጐጠ

ለጐ

ለገ/ማለገ

ለገ

ለገ

give; hand out

stick out (tongue/ mucus)

spit, throw lump

be slimy or viscous

stretch

track, trail

2ሀ

ምጥ

ማጠ፣ መጠጠ፣ መጠመጠ

የአየር/ የፈሳሽ ማለፊያ መጣበብና የግፊት/ስበት መፈጠር/መጠናከር

suction

2ለ

መጠ

መጠ

መጠ

eject

limit

sink, be sucked

3ሀ

ስል

ሳለ፣ ሰለለ፣ ሰለሰለ

መሳሳት፣ መቅለል፣ ማነስ፣ የአቅም መቀነስ

thinning, smoothing

3ለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

faint

grind fine

disappear

mild, soft

slither, slick

adapt

soften by cooking

4.ሀ

ርቅ

ራቀ፣ ረቀቀ፣ ረቀረቀ

ለአይን ማነስ፣ የውፍር መቀነስ፣ መሸራረፍ

fine grained

4ለ

ሰረቀ

ደረቀ

ፈረቀ

ooze

lose moisture

split

5ሀ

ቅር

ቀረ፣ ቀረረ፣ ቀረቀረ

ከመወሰድ፣ ከመቅቀነስ ተረፈ

refuse, hold out

5ለ

ቀረመ

ቀረሰ

ቀረበ

ቀረዘ

ቀረደ

ቀረጠ

glean

apportion

approach

hang to drop

tear off, slice

cut out, carve

6ሀ

ብዝ

በዛ፣ ባዘዘ፣ በዘበዘ

መዝዘርዘር፣ መመናታት፣ መትተንተን

multiplying, dividing

6ለ

ባዘተ

ባዘነ

ነበዘ

ደበዘ

thin out

be lost in thought

be unconscious

blur

7ሀ

ትል

ተላ፣ ተለለ፣ ተለተለ

ለጥቆ/ተያይዞ መሄድ፣ መከታተል

stream

7ለ

ባተለ

ከተለ

ፈተለ

be preoccupied

follow track

spin

8ሀ

ንፍ

ነፋ፣ ነፈፈ፣ ነፈነፈ

አየር/ንፋስ ገፋ/ሳበ

pump/ vacuum

8ለ

ነፈሰ

ነፈረ

ነፈጠ

blow

boil

blow nose

9ሀ

ክል

ከላ፣ ከለለ፣ ከለከለ

መልለየት፣ መከፈል

fence

9ለ

ተከለ

post

10ሀ

ውል

ዋለ፣ ዋለለ፣ ወለወለ           

መዘዋወር፣ መስፋት፣ መዝዘርጋት

wiggle, shift

10ለ

ወለቀ

ወለበ

ወለደ

slip off

flap

slip through

11ሀ

ዝል

ዛለ፣ ዘለለ፣ ዘለዘለ

ወደ ታች መሳብ/መውረድ

drop, hang

11ለ

ዘለመ

ዘለሰ

ዘለገ

pend

flop

stretch

12ሀ

ድል

ደላ፣ ደለለ፣ ደለደለ

ማሸራሸት፣ ማመቻቸት፣ እኩል ማድረግ

plain

12ለ

ደለቀ

ደለበ

ደለዘ

stomp

add layer

smudge

13ሀ

ግድ

ገሳ፣ ገሰሰ፣ ገሰገሰ

በግፊ መንሸራተት፣ መጋዝ            

move

13ለ

 

 

14ሀ

ጥፍ

ጠፋ፣ ጠፈፈ፣ ጠፈጠፈ

የገጾች መላተም፣ መለጣጠቅ

flap

14ለ

ለጠፈ

ቀጠፈ

ነጠፈ

paste

clip

flatten

15ሀ

ፍስ

ፈሳ፣ ፈሰሰ፣ ፈሰፈሰ           

 

የወላላ ይዘት (ውሃ፣ አየር፣ ጥሬ፣ ወዘተ.) ከመያዣው መውጣት፣ ማፈትለክ

leak, spill

15ለ

ለፈሰ

ነፈሰ

collapse

blow

ሠንጠረዥ፦ ከዘረቃል ወደ ሥርወቃል

 

ሁሉም የአማርኛ ቃላት ከቋንቋው የፍች-ተድምጽ ዘር ነስተው የተፈጠሩ አይደሉም። የድሃ አምዶችን መልክ ይዘው የሚቀረጹ፣ ፍቻቸው በድምጽ ከሚመስሏቸው ቃላት ያፈነገጠ ነባር ቃላት (ብዙዎቹ የአካል ክፍል ስያሜዎች ከነዚህ ይመደባሉ)፣ እንዲሁም ከዘመድም ሆነ ከባእዳን ቋንቋዎች በተውሶ እንደገቡ በአመጣጥ ታሪካቸው የሚታወቁ ብዙ ቃላት በውስጡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ የተውሶ ቃላት ስር ሰድደው ወልደውና ረብተው ሊገኙ ይችላሉ። ለነዚህኞቹ “ምስጢር” እና “ፊርማ” ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ስለዚህ ስርአተኞቹንና ዘረ ብዙዎቹን ስንተነትን እነዚህንም በጥንቃቄ ማስተዋል ይኖርብናል። 

ውሁዳን ዋለሎችን ለይቶ ስርወቃላትን ስለማግኘት፦ ከ“ስንፍና” ቅጥያዋን “ና”ን ገንጥለን አምደቃሉን “ስንፍ”ን እናገኛለን። መልከአምዱ ደጋሚም ሆነ ዋለል የማይጨምር ሁሉም ተናባቢዎቹ በሳድስ ተራ የሚገኙበት ነው። ስርወቃሉም የሶስቱ ተናባቢዎች ስድር [ስንፍ] ነው። በዚሁ አይነት “አሸናፊ”ን እንመልከት። ቅጥያዎቹን “አ”ን እና በ“ፊ” ላይ የምትታየውን የሳልስ ተራ ዋለል ጥለን አምደቃሉን “ሸናፍ”ን እናገኛለን። መልከአምዱ የግእዝና የራብእ ተራ ዋለል አናባቢዎችን የያዘ ነው። ስርወቃሉ [ሽንፍ] በዋለል [ይ] የቀለመች “ስ”ን ይዟል። እሷን ስንጥል ዘረቃሉን [ስንፍ]ን እናገኛለን። የ“ስንፍና”ም ዘረቃል ይኸው ነው። የ“መስነፍ”ን እና የ “ማሸነፍ”ን የፍች አንድነት በቀጥታ በመዝገበ ቃላት ሃተታ ባናገኘውም የ“መድከም፣ መዛል፣ ጽናት ማጣት” ሃሳብ እንደሚያገናኛቸው ማስተዋል ይቻላል። “ማሸነፍ” “ማስነፍ” ነው። እንደዚሁ “ሰፈነ”ን ከ“ሸፈነ”፣ “መጨነቅ”ን ከ“መጠንቀቅ”፣ “ተከለ”ን ከ“ቸከለ”፣ “እርጅና”ን ከ“አሮጌ” በስርወቃል ማገናኘት ይከብዳል?

ልክ እንደ “ስንፍና” ከ“ብልጽግና”ም “ና”ን ስንገነጥል “ብልጽግ” የሚል አምደቃል እናገኛለን። መልከአምዱም ልክ እንደ “ስንፍ” ደጋሚም ሆነ ዋለል የማይጨምር ሶስቱም ተናባቢዎቹ በሳድስ ተራ የሚገኙበት ነው። ይህን ቃል ለየት የሚያደርገው የስርወቃሉ የ[ብልጽግ] ፍች ተናባቢዎቹ በሌሎች ቃላት ውስጥ ካላቸው የፍች አስተዋጽኦ ተነጻጽሮ ሊገኝ አለመቻሉ ነው፤ ምክንያቱም በቀጥታ ከዘረቃላዊ ተናባቢዎች ስላልተመሰረተ ነው። ቃሉ ሃረጋዊ መሰረት አለው። ይህ አይነተኛ የቃል አመሰራረት ዘዴ አይደለም። “ባለ ጸጋ” ከሚለው ሃረግ [ብልጽግ] የሚል ስርወቃል ወጥቶ፣ በባለ ሳድስ ተራ መልከአምድ ተቀርጾ “ና” ሲቀጠልበት አዲስ ቃል ተፈጠረ። አቢይ ቃሉን “ጸጋ”ን ብቻ ይዘን ወደ ዘረቃሉ ስንወርድ (መሰረቱ አማርኛ  ከሆነ) ዘረቃሉ [ጥግ] ይሆናል። ከዚህ ዘረቃል የሚገኙ ቃላት “ጥግ”፣ “ጠገገ”፣ “ጠገረ”፣ “ጠገነ”፣ ወዘተ. እንደሚያመለክቱት የ‘ማልበስ’፣ የ‘መከለል’፣ የ‘መጠበቅ’ ስሜት ያለው ይመስላል።

ስርወቃላት ጥምር ቃላትን በማዋሃድም ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ “ደመወዝ” በግእዝ የጥምረት ስርአት ከ“ደም ወወዝ” የተፈጠረ ቃል ነው። እንደዚህ ያለውም የስርወቃል ፈጠራ አይነተኛ አይደለም። “ደም ወወዝ”ን ዛሬ “ደሞዝ” እየተባለ ብንሰማውም የፍች ጽንሱን [ድምዝ] ከሚል ስርወቃል ወይም [ድምዝ] ከሚል ዘረቃል አናገኘውም። ትንታኔው የ“ደም”ንና የ”ወዝ”ን ዘረቃላትና ሃረጋዊ ጥምረት ማገናዘብ አለበት። ባለብዙ ዘር ባለመሆኑ “ደም”ን በቀላሉ ከስርወቃል ልናገናኘው አንችልም። “ወዝ” ግን እንደ “ዋዛ”ና “ውዝዋዜ” ባሉ ቃላት እንደሚታየው ከዘረቃል [ውዝ] የወጣ ነው። በፍቹም “የንክኪን መለዘብና በቀላሉ መንቀሳቀስን” ያሳስባል።

አልፎ አልፎ ደግሞ ባልተሟላ የስርወቃል ፍለጋ ሂደት ከቃላቱ ላይ እንደ “መ” እና “ተ” ያሉ ቅጥያ ምእላዶችን ባለመግደፍ ከሚደረግ ትንታኔ ቅጥያዎቹን እንደስርወቃል ዛላ ይዘው የተገነቡ ቃላት አሉ። ለምሳሌ፦ ከ“ምርኩዝ” እና ከ“ተረከዝ” “መ” እና “ተ” ካልተነጠሉ [ረከዘ] በሚለው ስርወቃላቸው፣ “ቆንጥጦ፣ መድሮ መያዝ” (በእንግሊዝኛው anchor) በሚለው ረቂቅ ፍቻቸው ላይ የተመሰረተው የሁለቱ ቃላት አንድነት አይታይም። በነገራችን ላይ፣ የ[ክ←ግ]ን ውርርስ በማሰብ “አረገዘ”ም “ሽል ቋጠረ፣ ጽንስ ያዘ” የነዚህ ቃላት ወገን እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም።

ከ“ጤነኛ” ላይ “ኛ”ን ነጥለን ስርወቃሉን [ጥን]ን ወይም ዘረቃሉን [ጥን]ን እንደምናገኘው ከ“በሽተኛ” ላይ “ኛ”ን በመነጠል ስርወቃል አናገኝም። የ“በሽተኛ” መሰረት “በሽታ” ከአምደቃል “በሽ” እና ከቅጥያ “ታ” የተደራጀ ነው። የአምደቃሉ ጠባይ ከ“አለ” ጋር እየተቀናጁ ግስ እንደሚመሰርቱት እንደነ “ደስ”፣ “ዝም”፣ “ከፍ”፣ ወዘተ. ያለ ነው። ስርወቃሉ [ብስ] ዘረቃሉም [ብስ] ናቸው። የ “በሽታ” መነሻ “በሽ አለው” እንዲህ ፍቹ ሳይጠልቅና ሳይሰፋ ቀድሞ ቀላል ‘የሆድ መታወክ’ን የሚገልጽ ቃል ነበረ፤ ከ“(ሆድ) ባሰ”፣ “(አመለ) ቢስ”፣ “(ሆደ) ባሻ” እና ከመሳሰሉት ጋር ያወዳድሩት። በነገራችን ላይ የእንግሊዝኛው “disease”ም መሰረቱ “dis-ease” ቀላል የጤና መታወክ ነበር።

አንዳንድ ቃላት ከሌላ ሴማዊ ቋንቋ የተወረሱ ቢሆኑም ቀድሞ በአማርኛ ዘረቃላዊና ስርወቃላዊ መሰረት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ “ስልክ” ‘telephone’ን የሚሰይም፣ ‘ሽቦ’ ወይም ‘ክር’ የሚል ፍች ይዞ ከጥቂት አሰርት አመታት በፊት ከአረብኛ ቋንቋ የመጣ ቃል ነው። ነገር ግን “ስልክልክ”፣ “ሰልካካ”፣ “ሾለከ” በሚሉት ቃላት እንደሚታየው ስርወቃሉ [ሰለከ] የ ‘ሽቦ’ና ‘ክር’ን የፍች ስሜት ይዞ በአማርኛ ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉትን ቃላት የትውስት ታሪካቸውን ገልጾ ከነባር ዘረቃላቸው ጋር ማዛመድ ያስፈልጋል።

እንግዲህ የአፈንጋጭ ቃላቱን አመጣጥ ከዘረቃላዊው አመሰራረት አንጻር እንዲህ ከገለጥን ስርአታዊዎቹን ቃላት በዘር ለማገናኘት የሚያስፈልገው ከላይ በሰንጠረዡ በጥቅልሉ እንደታየው ቅሉ ተናባቢዎችን የሚጋሩ ቃላትን በፍች እያነጻጸሩ የሚስማሙትን በዘረቃልነት መያዝ ነው። የፍቺ ምርመራው ዘዴ ሳይንሳዊነት የጽንሰሃሳብ መግለጫዎቹን ከመወሰን አንጻር ፍጹም ባይሆንም የዘረቃላቱ ፍች  የብዙ ተዛማጅ ቃላትን መዝገበቃላዊ ፍች ከማነጻጸር የሚረቀቅ በመሆኑ አስተማማኝነቱ ከበቂ በላይ ነው። የአንድን ዘረቃል ፍች ለማርቀቅ ቢያንስ አምስት በስርወቃል ሃረግ የሚተሳሰሩ ቃላትን ማግኘት ያስፈልጋል።

የስርአታዊ ቃላቱን አመሰራረት ጥቂት ገባ ብለን ለማየት በዘወትር አገልግሎታቸውና አፈታታቸው የሚዛመዱ የማይመስሉ የሁለት ዘረቃላት ውሉዶችን እንመልከት። ዘረቃሎቹ [ብር] እና [ጥፍ] ናቸው። የተመረጡትም ዘረብዙ በመሆናቸው ነው። የ[ብር] ረቂቅ ፍች “ከፈተ፤ ገለጠ፤ ተላቀቀ፤ ተለያየ፤ በውስጡ አሳየ፣ አሳለፈ” ሲሆን ከውልድ ቃላቱ መሃል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ [በራ፣ በር፣ በረረ፣ በረበረ፣ በረቀ፣ በረከ፣ በረገ]።

የ “ብርሃን”ን ሃሳብ የያዙ ውልድ ቃሎች ሁሉ በተለያዩ አውደንባቦች የሚጨምሯቸውን ምስላዊነት/ ዘይቤአዊነት አካትቶ የፍች ጽንሳቸው “መግለጥ፣ መክፈት፣ ማሳየት” ነው። “ዝናቡ በራ/አባራ፣ ብራ ሆነ” ማለት “ወጣ፣ ገለጠ” ማለት ነው። “በር”ም “የተከፈተ፣ መውጫ” ማለት ነው። “መብረር”ም በ“ር” መደገም መራቅን እና ቀጣይነትን አክሎ የ“መላቀቅ”ን፣ “ተለይቶ የመሄድ”ን ረቂቅ ሃሳብ ይገልጻል። “መበርበር” “መግለጥ፣ መክፈት፣ ውስጥን ማየት” ነው፤ የድርጊቱ ጥልቀትና ቀጣይነት በዘረቃሉ መደገም የተገኘ ነው። “በረቀ” “ድንገተኛ የብርሃን መገለጥ”ን ረቂቅ ሃሳብ ይይዛል። ከዚህ ዘረቃል የሚወጡት “መብረቅና” “ብርቅ” በመጀመሪያ እይታ የሚገናኙ አይመስሉም። ግን ቀስ ብለን ብንመረምር “ብርቅ” ማለት “እንደልብ የማይገኝ፣ ውድ፣ የከበረ ዋጋ የሚሰጠው፣ ከዚህም የተነሳ ደብቀን የምንጠብቀውና ለአንድ አፍታ ብቻ ገልጠን የምናየው/የምናሳየው ነገር” ነው። ከ“መብረቅ” ጋር የሚያዛምደውም ለአንድ አፍታ ብቻ ተገልጦ መታየቱ ነው። “መብረቅረቅ”ም በደጋሚ አምደቃሉ ከሚጨምረው የእይታ ድግግሞሽ በቀር የያዘው ያው የ“ድንገተኛ ብርሃን መገለጥ”ን ሃሳብ ነው። “በረከ” እና “በረገ”ም በየውልድ ቃሎቻቸው የያዙት ረቂቅ ሃሳብ “ከግንኙነት ጽናት ማጣት፣ ድንገት መከፈል፣ መለየት” ነው። 

የ[ጥፍ] ረቂቅ ፍች “ሁለት ገጾችን/ፊቶችን አማታ፣ አገናኘ፣ ገጠመ” ማለት ሲሆን፣ ከውልድ ቃላቱ መሃል የሚከተሉት ይገኛሉ፦  [ጠፋ፣ ጣፈ፣ ጠፈፈ፣ ጠፈጠፈ፣ ነጠፈ፣ አነጠፈ፣ ተንጠፈጠፈ፣ ለጠፈ፣ አጠፈ፣ ቀጠፈ፣ ዘነጠፈ]።

“መሰወር” የሚለው የ “መጥፋት” ፍች ቀጥተኛ አይደለም፤ “ሁለት ገጾችን ማማታት” የሚያስከትለው ‘ስውር’ ፍች ነው፤ በአንዱ ወይም በሁለቱም ተጋጣሚ ገጾች ላይ ያለ ምስል ወይም ቀለም ይሰወራል። “በጥፊ መታ” የሚለው ፍች ግን በድምጽ ስሜቱም ጭምር በቀጥታ የሚመስለው ነው። “(ቀዳዳ) መጣፍ፣ መጠፍጠፍ፣ መለጠፍ” እነዚህም ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። “መንጠፍ” “ይዘትን አፍስሶ/ አውጥቶ ከመጨረስ የሚመጣ “መሰለግ፣ የውስጥ ገጽ መጣጋት” ነው። “መንጠፍጠፍ”ም በአምደቃሉ ይለይ እንጂ ያው “መንጠፍ” ነው። “መለጠፍ” እና “ማጠፍ” በፍቻቸው “የገጾችን መላተም” በቀጥታ ያሳያሉ። “መቅጠፍ” በጥቂቱ/ በአጭሩ፣ እንዲሁም “መዘንጠፍ” በስፋት/ በረጅሙ “አጥፎ መቁረጥ”ን ሲያመለክቱ “የገጾችን መጋጠም” በቀጥታ እናየዋለን።

በመጨረሻም በተከተልነው የትንተና ዘዴ “ነጋዴ”ን፣ “እንግዳ”ን፣ “ነገድ”ን እና “መንገድ”ን በ[ንግድ] ማገናኘት ፈታኝ አይሆንም። የስርወቃሉን ፍች መወሰንስ? ምናልባት የ “ነጋዴ” እና የ “ነገድ” ፍችዎች ትንሽ ይርቁብን እንደሆን እንጂ በያዝነው የፍች ምልከታ ሌሎቹን በቀላሉ ከ “መሄድ፣ መጓዝ” ጋር እናገናኘዋለን። እርግጥ ነው ቆም ብለን ካላሰብን በዘወትር እይታችን “እንግዳ”ን ከ “መንገድ” አናገናኘውም፤ በባህላችንም መንገደኛ እንግዳ ማስተናገዱ እየቀረ ስለሆነ። “ነጋዴ”ም “ነጓጅ፣ ተጓዥ፣ ወራጅ”፣ “ነገድ”ም “የትውልዶች ተዋርድ፣ የክትትል ጉዞ” ናቸው። የስርወቃሉም ፍች ሲጠቃለል “ተከታትሎ መሄድ፣ መውረድ” ይሆናል። እንግሊዝኛውም ይህን መሰረታዊ ፍች በአንድ ዘረቃል ይወክላል በ[tr]: tribe, trade, track, trip, travel, train, trend, … የቃላት ፍች ምርመራ አቅማችንን ለማነቃቃት እስካሁን ያየነው ይበቃል።

እንደዚህ በብዙ ስርወቃላት ውስጥ የሚገኙ ባለሁለት ተናባቢ ዘረቃላትን እየለየን ፍቺዎቻቸውን ካረቀቅን፣ ደግሞ ከዚያ ዘልቀን እያንዳንዱ ተናባቢ በየዘረቃሎቹ የሚያበረክተውን የፍች አስተዋጽኦ የዘረቃላቱን ፍች በማወዳደር አንጥረን ማውጣት እንችላለን። በዚህ አይነት የአስራ ስድስቱም የአማርኛ ቅሉ ተናባቢዎች ረቂቅ ፍች ይወሰናል። በያንዳንዱ ቃላት ውስጥ በስርወቃላቱ በኩል የፍች መሰረት ሆነው የሚገነቡት እነዚህ የተናባቢዎቹ ረቂቅ ፍችዎች ናቸው። እንዲህ ነባር ቃላትን በያዟቸው ድምጾች አይነትና ሰልፍ እያነጻጸርን የፍች ዝምድናቸውን መመልከት ከቻልን አዳዲስ ውልድ ቃላትን በቅድሚያ ከስርወቃላት ሲያልፍም ከዘረቃላት ለመፍጠር ጽኑ መሰረት አገኘን ማለት ነው። አዳዲስ ቃላትን ለማግኘት ነባሮቹንና የአፈጣጠር ስርአታቸውን ጠለቅ ብሎ መመልከት እንጂ ከሌሎች ቋንቋዎች ለማምጣት አሻግሮ መመልከት አያስፈልግም።

ከመሰናበቴ በፊት በቀዳሚው ጽሑፌ እንዳመለከትኩት በጥቂቱ ለማሳየት የሞከርኩትን የፍች ምርመራና የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በሰፊው አሳውቄ ታታሪ የሆኑ ግለሰቦችን በማስተባበር የአማርኛን ልማት ለመምራት ተነስቻለሁ። ለዚህም ስለአማርኛ ቋንቋ ልማት ሃሳብ ለመለዋወጥ የሚያግዝና በቀጥታ ቃላትን በመፍጠር፣ በማከማቸትና በማሰራጨት ተግባዊ እንቅስቃሴው የሚከናወንበት በhttp://amharic-language.com አድራሻ የሚገኝ ድረገጽ በቅርቡ እከፍታለሁ። ድረገጹን እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ። አስተያየቶቻችሁን በ btadata@gmail.com ብትልኩልኝ በደስታ እቀበላለሁ።

ኑ! አማርኛን እናሰልጥን!

በዛ ተስፋው አያሌው   

| pdf | አስተያየት

አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን! [ክፍል አንድ]

አማርኛ ከዘመናዊው አኗኗርና አስተሳሰብ በተለይም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በብቃት አብሮ ሊራመድ አለመቻሉ በተለይ አሁን በዘመነ ‘ኢንተርኔት’ እጅግ አግጥጦ የወጣ ሃቅ ነው። አገሪቱም ለአማርኛ ቋንቋ የልማት እቅድ የላትም። የተያዘው የደመነፍስ ጉዞ የተቻለውን በአማርኛ የልተቻለውን በእንግሊዝኛ እያደባለቁ መሄድ ነው። የዚህ አካሄድ መድረሻው ለብዙዎቻችን የተሰወረ አይደለም። በሌላ በኩል በህሊና እንመራ የሚሉ ጥቂት ዜጎች ዘመናዊ አስተዳደር ወደአገሪቱ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ዘመናዊውን አኗኗር በአማርኛ የመምራትን አስፈላጊነት ተገንዝበው ሰዋስዉን በማተትና መዛግብተ ቃላትን በማጠናቀር አማርኛን ለማዘመን ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል፤ የቋንቋውን የልማት ጎዳና ጠርገዋል።

በመሃሉም በመንግስት ትእዛዝና ድጋፍ እንዲሁም በታላላቅ ምሁራን ተሳትፎ በተከወነ ትልም በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽንሰሀሳቦች መተርጎሚያ ይሆናሉ የተባሉ የአማርኛ ቃላት ተፈጥረው በመዛግብተ ቃላት ታትመዋል፤ መልካም ጅምር ቢሆንም ሁሉም እንደሚያውቀው ውጤቱ ያልጠቀመ በከንቱ የቀረ ትልም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አማርኛን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ የማድረግን አስፈላጊነት የሚለፍፉ ጩኸቶች ተበራክተዋል፤ አርአያነት ያላቸው ጥቂት የግል ጥረቶችም ታይተዋል። እዚህ ላይ ጥርጊያውን መንገድ ይዞ፣ ከውድቀት ተምሮና የወገንን ተነሳሽነትና አስተዋጽኦ አለኝታ አድርጎ ዘላቂ ትልም ማበጀት ያስፈልጋል። እኔም በዚህ አጋጣሚ በስነልሳን ተማሪነቴ የበኩሌን ለማድረግ ድምጼን ከማሰማት ባለፈ ለአንድ አሰርት አመታት ያህል ባደረግሁት ምርምር ያገኘሁትን እጅግ ጠቃሚ የምለውን የቃላት ፍች ምርመራና የአዳዲስ ቃላት አፈጣጠር ዘዴ ለማካፈልና የሌሎችንም ታታሪ ግለሰቦች ተግባራዊ አስተዋጽኦዎች በማስተባበር የአማርኛን ልማት ለመምራት አቅጃለሁ።

 

እቅዴን ለማስተዋወቅ መነሻ እንዲሆነኝ ስለአማርኛ መሰልጠን አስፈላጊነት በጽኑ አምነው (እኔ በማውቀው ከዛሬ ሰባትና ስምንት አመታት ጀምረው) የፈጠሯቸውን ቃላት እያስተዋወቁ የ’አማርኛ ይሰልጥን’ ጥሪአቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙትና ስለጉዳዩም ጥሩ ውይይት ያስጀመሩት ዶ/ር መስፍን አረጋ አማርኛ አሁን ስላለበት ሁኔታ የሰጡትን አጭር ግምገማና መፍትሔ ያሉትን የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በመቃኘት እጀምራለሁ። በተለይ “ሰገላዊ አማረኛ (አማሮምኛ)” በሚል ርእስ በተለያዩ ድረገጾች ያወጡት ጽሑፍ መሪ ሃሳባቸውን የያዘ ነው። ዋና ዋና ነጥቦቹ እንደሚከተለው ይጠቃለላሉ፦

  • አማርኛ እንግሊዝኛ ባደረሰበት ጥቃት ተዳክሞ ወደ መጥፋት እየተቃረበ ይገኛል ይላሉ። የጥቃቱንም ሁኔታ በወታደራዊ አቋምና በጦርነት ይመስሉታል።
  • ለጥቃቱ መሪና አባሪ የሆኑትም ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ባለስልጣኖች ናቸው ሲሉ ይከስሳሉ።
  • እሳቸው ‘መሰሪ’ ያሉት የነዚህ ወገኖች የጥፋት ስልትም ተራውን ህዝብ የራሱን ቋንቋ ንቆ እንግሊዝኛን እንዲያከብር ማሳመን ነው።
  • በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አማርኛን እንዳይናገሩ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው የልጆችን ስም እንዲሁም የማእርግ፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የህንጻዎች፣ የሸቀጦች፣ ወ.ዘ.ተ ስሞችን ከአማርኛ ይልቅ በእንግሊዝኛና በሌሎች የውጭ ቋንቋዎች መሰየሙ ራስን የመናቅና ማንነትን የማጣት መታያዎቹ ናቸው ይላሉ።
  • ታላላቅ የቀድሞ የአማርኛ ቋንቋ ሊቃውንትን ጠቅሰው አማርኛን ለጥቃት ያጋለጠው እንደነዚያ ያሉ ጠባቂዎቹን በማጣቱ ነው ሲሉ ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።
  • የአማርኛ ጥፋት የኋላ ኋላ የማህበረሰቡ ማንነት ጥፋት ስለመሆኑ ያስጠነቅቃሉ።
  • በመጨረሻም አማርኛ በአለም ከሚገኙ አበይት ከሚባሉ ቋንቋዎች አቻ ከመሆንም አልፎ በብዙ እጥፍ ሊበልጥ የሚያስችለው ስርዓት እንዳለው ይጠቁሙና፣
  • አማርኛን ለማዳን አሁን የሚያስፈልገው የተዛባውን ስርአቱን ማስተካከልና አዳዲስ ቃላትን መፍጠር ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ። አዳዲስ ቃላትን የመፍጠሪያው ዘዴም ከአማርኛ ስርአት ጋር እያስማሙ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች መቅዳት ነው ይላሉ። በዚህ አይነት ራሳቸው የአማርኛን ቃላት (በተለይ)፟ ከኦሮምኛ ቃላት ጋር በማዳቀል ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እሳቤዎች መወከያ የፈጠሩትን የቃላት ስብስብ ‘አማሮምኛ’ ወይም ‘አማሮሚፋ’ ይሉታል። ያዘጋጁትን የቃላት ስብስብና የቃላት አፈጣጠሩን ዘዴ ቢቀበሏቸው ኢትዮጵያውያን በራስ መተማመንንና ታላቅነትን መልሰው እንደሚቀዳጁ ይመክራሉ።

 

ዘርዘር አድርገን ስንመለከት፣ እንግሊዝኛ በአማርኛ ላይ ስላደረሰው በደል ያስረዱበትን ተውኔታዊ ገለጻ የተጠቂነትን አስተሳሰብ ለማጕላትና አንባቢን በቁጭት ለማነሳሳት የተከተሉት የአቀራረብ ዘይቤ ነው ብለን እንተወው። እውነት ግን አማርኛን ያቈረቈዘው እንግሊዝኛ ነው? አይደለም! የአማርኛ ባለቤቶች ለራሳቸው ካለማወቃቸው፣ በተለይም ከሌላው አለም የሚመጣውን የዘመናዊነትን እውቀትና ብልሃት ከባህሪው አስማምቶ እንዲቀበል፣ ለዘለቄታውም የእውቀትና የብልሃት ፈጠራ መሪና ዘዋሪ እንዲሆን ቋንቋቸውን ለማመቻቸት ካለመትጋታቸው የተነሳ፣ ከሸቀጥ ጋር ስሙን፣ ከአስተሳሰብ ጋር ብሂሉን (በተለይ) ከእንግሊዝኛ ወደአማርኛ እየሰገሰጉ የቋንቋቸውን የመፍጠር አቅም አዳከሙት እንጂ እንግሊዝኛ ቋንቋ በአማርኛ ላይ ያደረሰው ጥቃት የለም። እንዲያውም የአማርኛ ባለቤቶች ቢያውቁበት እስካሁን ሳይንስ የከሰተውን ሩቅና ረቂቅ አለም ለመመልከት እንግሊዝኛ መነጽራቸውና መንገድ መሪያቸው ነበር። እዚህ ላይ ሰዎች እንጂ ቋንቋዎች እንደማይጠቃቁ ጸሐፊው ያስቱታል ብዬ አይደለም። ነገሩ ራስን ከመጣል እንጂ ከተጠቂነት አንጻር መቅረብ የለበትም ለማለት ነው።

 

እንግሊዝኛን በጠላትነት በማየት አማርኛን አንታደገውም። ታላቅነቱንና ሃያልነቱን እንዴትም ያግኘው፣ እንግሊዝኛ ዛሬ ታላቅና ሃያል ቋንቋ ነው። እርግጥ ነው እንግሊዝኛ አሁን አለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት እንደማንኛውም ቋንቋ እንደነበረ ማስታወሱ አማርኛም የመላቅና የማየል ተስፋ እንዳለው በማመልከት ቀናእያን ዜጎችን ለቋንቋቸው ማደግ እንዲጥሩ ያነቃቃል። ሆኖም እንግሊዝኛ ድንገት ተነስቶ ከሌሎች ቋንቋዎች ቃላትን አግበስብሶ እንደዳበረና እንዳየለ አድርጎ ማቅረቡ ግን እውነተኛውንና ብናውቀው የሚጠቅመንን የእድገቱን ምስጢር ከራስ መሰወር ይሆናል። እንግሊዝኛ ከሚዘውረው ስልጣኔ ጋር በታታሪ ባለቤቶቹ ብርቱ ጥረት ተከብክቦ የዳበረ ቋንቋ ነው። ይልቅስ እንግሊዝኛ ለዛሬው አቅሙ የበቃበትን የእድገት ሂደቱን መርምሮ ለአማርኛ ማሰልጠኛና ማዘመኛ የሚረዳውን ብልሃት መቅሰም ይበጃል። 

 

‘አማርኛን ያዳከመው የኢትዮጵያውያን ምሁራንና ባለስልጣኖች መሰሪ ተግባር ነው’ ማለት የባለስልጣኖችንና የምሁራንን የአገር ራእይ ቅድስና የሚገመግም አስተያየት ነው። መነሻ ሀሳባችን ‘ባልስልጣኖችንና ምሁራንን ጨምሮ ባለአገሮቹ አገራቸውን የሚያለማ እንጂ የሚያጠፋ ራእይ ይዘው አይነሱም’ ነው። ወደተሻለ መደምደሚያ ባያደርሰንም ነገሩን እንዲህ ብንመለከተው ይሻላል። ከጅምሩ የትናንት ህጻናት የዛሬዎቹ ባለስልጣኖችና ምሁራን፣ በአገር ውስጥም  ሆነ ወደውጭ አገር እየተሻገሩ የምእራባውያንን ስልጣኔና ዘመናዊውን እውቀት በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲቀስሙ ሲደረግ፣ በቀዳሚነታቸው የተማሩትን ለተከታዮቻቸው በአማርኛ ቋንቋ እያስተማሩ የኋላ ኋላ አማርኛ ራሱን ችሎ የዘመናዊ እውቀት መዘውር እንዲሆን ቋንቋውን የማሰልጠንና የማዘመን ስራ በእቅድ አልተሰራም። በዚህ እቅድ መጕደል የተነሳ የኑሮ ልማዶቹን በዘፈቀደ ‘ማዘመን’ የጀመረው አገሬው፣ ቋንቋውንም እንደአሮጌዎቹ ልማዶቹ እየተወ እንግሊዝኛን እየተቀበለ አዘገመ። ጊዜውም ረዘመና ይኸው ዛሬ ተራና የዘወትር የሚባሉ ሃሳቦችን እንኳ በአማርኛ ቃላት መግለጽ እስከሚቸግር ድረስ አማርኛ ደበዘዘ። ይህን ችግር ባለስልጣኖችና ምሁራን በመሰሪነት ባያመጡትም በግዴለሽነትና በንዝህላልነት እንዲንሰራፋ በመተዋቸው ወቀሳው አይቀልላቸውም።

 

በሌሎች አበይት የኑሮ ዘርፎች አማርኛ እስካሁን ተገልሎ የቆየባቸውን አገልግሎቶቹን ትተን ዶ/ር መስፍን ያነሷቸውን ጥቂቶቹን ብንመለከት፦ አዎ ዛሬ ህጻናቱ፣ የንግድ ተቋማቱ፣ የወታደርና የፖሊስ ማእርጎች፣ ወዘተ. በአማርኛ መሰየማቸው ቀርቶ በእንግሊዝኛ እየሆነ ነው። ግን ሊያስደንቀን አይገባም። እንግሊዝኛ ቋንቋን ‘በጥራት ለማስተማር’ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ልጆች ከእንግሊዝኛ በቀር አማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ የሚያሳፍሩና የሚያሸማቅቁ ማስታወቂያዎች እየተለጠፉና እየተለፈፉ ነው። ይህም ሊያስደነግጠን አይገባም። በግልጽም ሆነ በስውር ብዙው ሰው ‘በዘመናዊ ኑሮ አሸናፊ ለመሆን ዋነኛው መሳሪያ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እውቀት ነው’ ብሎ ያምናልና። አማርኛ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳለ ይህን እምነት በቀጥታ መጋፈጥ አይቻልም። አማርኛ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳለ የተዘረዘሩትን የማንነት ቀውስ ምልክቶች እያነሳን ሰዎችን “ማንነታችሁ ነውና አማርኛችሁን ጠብቁት” በማለት የለውጡን ሂደት አንገታውም። የማንነታቸው ጥፋት ሰዎችን ስለማያሳስባቸው ሳይሆን የጥፋቱ ሂደት በጣም አዝጋሚና ወዲያው የማይታይ በመሆኑ በግሉ የኑሮ እሽቅድድም የራስን ደረጃ ለማሻሻል ከመፍጨርጨር አልፈው የጋራ ለሆነው ማንነት ተገቢውን ትኩረት ስለማይሰጡት ነው። ስለዚህ እንደኢኮኖሚው ልማት ሁሉ አማርኛን በማሰልጠን ለዘመናዊ አኗኗር ብቁ መሳሪያ የማድረጉ አስፈላጊነት በጽኑ ሊታመንበት የሚገባው በመንግስት ባለስልጣኖችና በምሁራን ነው።

 

ምሁራንና ባለስልጣኖች ቋንቋቸው ሰልጥኖ ለዘመናዊ አስተሳሰብና አኗኗር ብቁ መሳሪያ ቢሆን የሚገኘውን ጠቀሜታ አይስቱትም። ጉዳዩ ለተግባሩ አፈጻጸም እስካሁን አስተማማኝ ዘዴ አለመኖሩ ነው። ዶ/ር መስፍን የሳይንስና የቴክኖሎጂ እሳቤዎችን የሚወክሉ የአማርኛ ቃላትን ለመፍጠር ያስችላል ያሉት የአማርኛ የቃል ዘሮችን ከኦሮምኛ ወይም ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የቃል ዘሮች ጋር የማዳቀል ወይም አዳዲስ የቃል ዘሮችን ወደአማርኛ የማስገባት ዘዴ (ምንም እንኳ ቃላቱ በአማርኛ ቋንቋ ስርአተ ቃላት እንዲዋለዱና እንዲረቡ ሆነው ቢፈጠሩም) ከነባሮቹ ቃላት ጋር ጥልቅ የድምጽና የፍች ትስስር የማያሳዩ ባእድ ቃላትን የሚያበዛ ነው[1]። ከሌላ ቋንቋ በማዳቀል የሚፈጠሩትም ሆነ በቀጥታ የሚገቡ ቃላት ለአስተናጋጁ ቋንቋ በሁለመናቸው እንግዳ ናቸው። ስለዚህ ለመለመድ በጣም አዳጋች ይሆናሉ። አዳዲስ ቃላት በቀላሉ የሚለመዱት ከነባሮቹ ቃላት ጋር ሊመረመር የሚችል ስርአታዊ የፍችና የድምጽ ትስስር ሲኖራቸው ነው። የቃላት አፈጣጠሩ ዘዴም ይህን እውነት ያገናዘበ መሆን አለበት። ዶ/ር መስፍን በተለይ ከኦሮምኛው ጋር የማዳቀሉን ሃሳብ በባህል ማስተሳሰሪያነቱና በፖለቲካ ውጥረት ማርገቢያነቱ አይተውት በልዩ ልዩ የሳይንስ ዘርፎች ያላቸውን እውቀት ተመርኩዘው በብርቱ ትጋት በርካታ ቃላትን ፈጥረው ቢያሳዩንም፣ በመሰረቱ የተከተሉት ዘዴ የአማርኛ ቋንቋን ስነሕይወት በጥልቀት ያላገናዘበ ነው። እንዲህ ባእድ ቃላትን እየፈጠሩና እየተዋሱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እሳቤዎችን የመሰየሙ አካሄድ በሌሎችም የቋንቋ ልማት ጥረቶች ተሞክሮ ምንም ያህል አላራመደም።

 

ቋንቋን የማዘመንን ዘዴ በቀጥታ ከእንግሊዝኛ ልንቀዳው አንችልም፤ ምክንያቱም እንግሊዝኛ በእቅድ አልዘመነም። የዘመናዊነት ለውጥ ጅምሩ ከታየ በኋላ ግስጋሴው በአስተውሎት መታገዙ ባይቀርም፣ የምእራቡ አለም አኗኗር ወደዘመናዊነት የተሸጋገረው በተፈጥሮአዊ ሂደት እንጂ እንደኛ አርአያ ተከትሎ ‘ልማት’ ተብሎ ታቅዶለት አይደለም። የእንግሊዝኛ ዘመናዊነትም በአብዛኛው እዚያው በኑሮው ለውጥ መሃል የሆነ ነው። በታቀደ ልማት በአፋጣኝ ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር የሚያልሙ ማህበረሰቦች ግን እውቀትን የልማታቸው ሃይል ማድረግ የሚሹ ከሆነ ለቋንቋቸውም መዘመን የልማት እቅድ ሊያበጁለት ይገባል። በተፈጥሯዊ ሂደት የዘመኑትን የምእራባውያን ቋንቋዎችን አስተዳደግ ከመመርመር ቋንቋ እንዴት እንደሚለማ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ዋናው ምርምር ግን የራስን ቋንቋ ተፈጥሯዊ የፈጠራ አቅም እማወቅ ላይ ማተኮር አለበት። ሆኖም ጥቂት የማይባሉ የምሁራን ትውልዶች ያለፉበት በአብዛኛው የአውሮፓውያን ቋንቋዎች ጥናት ባስገኘው ስነዘዴ ላይ የተመሰረተው ዘመናዊው የቋንቋ ጥናትና ምርምራችን ክፋቱ፣ አማርኛ ቋንቋ ስርወቃላትን ከ(ምስረታና እርባታ) አምዶች ጋር አስማምቶ በአምደቃላቱ ላይ ምእላዶችን ከመለጠቅ፣ ወይም ቃላትን ከቃላት ከማጣመር ያለፈ የቃል ፈጠራ አቅም እንዳለው አላስገነዘበንም። የአማርኛን የቃል ፈጠራ አቅም ለመገንዘብ የሚያስፈልገው የስርወቃላቱን ረቂቅ ፍች አንጥሮ ማውጣትና ስርወቃላቱ የተመሰረቱባቸውን ድምጾች የፍች አስተዋጽኦ መመርመር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ታዲያ በትምህርት ቤት ቆይታዬ ከተለመደው የቃላት ምስረታ ትንታኔ ላፈነገጡ የቃላት ግንኙነቶች ተስማሚ ማብራሪያ ሳፈላልግ የተከተልኩት አግጣጫ የአማርኛ ቃላትን የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ ዘልቄ እንድመለከት አስቻለኝ። እንግዲህ ይህን የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ ነው የአማርኛ ድልብ የቃላት ፈጠራ አቅም ነው የምለው። ወደዚህ ግኝት እንዴት እንደደረስኩ ከዚህ በታች በአጭሩ አስረዳለሁ። ግኝቱም ለቃላት ፈጠራ እንዴት ሊውል እንደሚችል በተከታይ ክፍል እመለስበታለሁ።

 

መጀመሪያ ቀጥተኛ የስርወቃል ዝምድና በሌላቸው የአማርኛ ቃላት መካከል የድምጽና የፍች መቀራረብ እንዳለ አስተዋልኩ[2]። ከዚያም በጠቅላላው በቃላት ውስጥ የሚታየው የድምጽ-ተፍች ጥምረት መነሻው ከስርወቃላት ዝቅ ባለ ደረጃ ይጀምራል ከሚል መላምት ደረስኩ። በምርምሬ ሂደትም በልቡናዬ ከስርወቃል በሚፈጠሩ ቃላት ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ድምጽ ለሚገነባው ቃል ረቂቅ የፍች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተሰማኝ። ከዚህም ተነስቼ ድምጾች በተናጥልና በጥምረት የሚኖራቸውን ረቂቅ የፍች አስተዋጽኦ 1ኛ) የባለሁለት ተናባቢ ሁለት ዛላ (ምሳሌ፦“ዛለ”) ስርወቃላትን ረቂቅ ፍች ከባለሁለት ተናባቢ ሶስት ዛላ (ምሳሌ፦”ዘለለ”) እና አራት ዛላ (ምሳሌ፦ “ዘለዘለ”) ስርወቃላት ጋር በማገናዘብ 2ኛ) የያንዳንዱን ድምጽ ረቂቅ ፍች በመጀመሪያ ያንኑ ድምጽ በመድገም ከሚፈጠሩ ባለአንድ ተናባቢ ሁለት ዛላ (ምሳሌ፦“ዛዛ”፣”ላላ”) ስርወቃላት፣ ከዚያም ያንን ድምጽ ከሚይዙ ተዛማጅ ባለብዙ ተናባቢና ባለብዙ ዛላ ስርወቃላት ጋር በማገናዘብ አንጥሮ ማውጣት እንደሚቻል ተመለከትኩ። ከዚያም ረቂቅ ፍቻቸው የተለዩት የሁለት ተናባቢ ቅንጅቶች በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ በበቂ ድግግሞሽ በባለሶስትና በባለአራት ዛላ ስርወቃላት (ምሳሌ፦ “ዘለ” በ“ዘለመ” እና በ“ዘለበደ”) ውስጥ ሲገኙና አቃፊዎቹ ስርወቃላት የታቃፊዎቹን ረቂቅ ፍች ሲጋሩ ከመመልከት፣ የአማርኛ ቃላት የፍች ትስስር ሃረጋቸው ከስርወቃል ወርዶ እስከ ጥምርና ነጠላ ድምጾች ደረጃ እንደሚዘልቅ ተገነዘብኩ። ይህ የድምጽ-ተፍች ጥምረት ክሳቴ ከራሴ የግል ስሜትና ካደረግኩት ትንታኔ አልፎ በቋንቋው ተናጋሪዎች ልቡና ይኖር እንደሆን ለማወቅ ባደረግኩት መጠይቃዊ ቅኝት በአስተማማኝ መጠን ማረጋገጫ አግኝቼበታለሁ።

 

ከዚህ ግኝት በመነሳት የቃላት ግንባታውን ስርአት እንደሚከተለው ማደራጀት ይቻላል። ለቃላት የድምጽ-ተፍች ጽንስ የሆኑትን ጥምርና ነጠላ ድምጾች[3] ዘረቃል ብንላቸው፣ ዘረቃላቱ በተጨማሪ ድምጾች እየተጎላመሱ ስርወቃላትን ይፈጥራሉ፤ ስርወቃላቱ ደግሞ በስነምእላዳዊ ሂደት ለቃላት ግንባታ መሰረት ይሆናሉ። እንግዲህ አንድም የቃላትን የፍች መሰረት እስከዘረቃላት ድረስ ወርደን መረዳት እንችላለን፤ ሁለተኛም የቃላት ምስረታ በነባር ስርወቃላት ብቻ እንደማይወሰን እናምናለን፤ በፍቻዊ መሰረታቸው እንግዳ ያልሆኑ አዳዲስ ስርወቃላትንም መፍጠር እንችላለን ማለት ነው። በርግጥም በዚህ አይነት የቃላትን ረቂቅ ፍችዎች በጥልቀት መመርመርና አዳዲስ ስርወቃላትን ከቋንቋው ስርአት ሳይወጡ መፍጠር ከተቻለ በትውስት ቃላት ተደንግሮ የቆመው የቋንቋው ተናጋሪዎች ምናብም ይነቃና እሳቤዎቹን በቋንቋው መሰየሙን ይቀጥላል። ዶ/ር መስፍንም ጥልቅ የሳይንስ እውቀትዎን፣ ልዩ የቋንቋ ችሎታና አስተውሎትዎን፣ የማይበገር የስራ ትጋትዎን፣ እንዲሁም ነዲድ የአገር ፍቅር ስሜትዎን ይዘው አሁን ያስተዋወቅሁትንና በተከታይ የማብራራውን አዲስ የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በጥሞና እንዲገመግሙና አስተያየትዎን እንዲሰጡ እጋብዛለሁ። ከዚያም የአማርኛን ስነሕይወት በጥልቀት ባገናዘበ ሁኔታ በብሩህ ምናብዎ አዳዲስ ቃላትን እየፈጠሩ በቅርቡ በሚመሰረተው የ’አማርኛን እናሰልጥን’ ህብረት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ። በተከታዩ ጽሁፌ የቃላትን የፍች ግንኙነት ትንታኔ በምሳሌዎች አስረዳለሁ።

 

ሰላም!

በዛ ተስፋው

     

 

[1] እዚህ ላይ የዶ/ር መስፍን ጽሁፍ በየድረገጹ ታትሞ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ በነበረበት ጊዜ ፍሥሓ የተባሉ አስተያየት ሰጪ የቃላት ፈጠራው ዘዴ “ዛሬን ከትናንትም ከነገም፣ ትውልዱን ከአበውም ከውሉድም፣ የማይለይ …” ይሁን ያሉትን፣ እንዲሁም ቦጋለ ዳኜ የተባሉ አስተያየት ሰጪ “አንዳንድ ጊዜ ቃላቱን በቀላሉ ለመያዝ በውስጣቸው ያለው መነሻ ዘር ስለማይታወቅ ማስታወስ ይቸግራል።” ማለታቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል።

[2] ይህ ሁነት በሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎችም በተወሰነ ደረጃ ስለመታየቱ ቀደም ያሉ ሊቃውንት የገለጹ ቢሆንም በየትኛውም ቋንቋ ጥልቅ የቃላት ግንኙነት ስርአት ስለመሆኑ በአግባቡ ተመርምሮ አልታየም።

[3] በነገራችን ላይ የዚህን ግኝት ንደፈሃሳባዊ ዋንነት ለመመልከት የስነፍች መሰረታዊ አሃዶች (semantic atoms) ባልተለዩበትና ንድፈሃሳባዊ ብያኔ ባላገኙበት የቋንቋ ጥናት ሳይንስ ነጠላ ድምጾችን አላባዎች (elements)፣ ጥምሮቹን ደግሞ ውሁድ (compound) ልናደርጋቸው እንችላለን። ቃላት ቁሳዊም ሆነ ፍቻዊ ባህርያቸውን የሚወርሱት በውስጣቸው ካሉት አላባዎችና ከአደረጃጀታቸው ነውና።

| pdf | አስተያየት