በየማኅበራዊ መገናኛዎችና በሌሎችም የአስተያየት መስጫ ‘ድረገጾች’ ላይ ‘like’ እና ‘unlike’ ደምበኛ የአስተያየት ህዝበኝነት (ተወዳጅነት) መመዘኛ ቃላት ሆነዋል። እነዚህ ቃላት እንዳሉ ወደአማርኛ ገብተው “እባካችሁ ይህን ድረገጽ፣ አስተያየት፣ ወዘተ. ላይክ አድርጉት” እየተባለ ሲጻፍ እናያለን። መተቸቱን ትተን በመፍትሔው ላይ ለማተኮር፣ በአማርኛ ‘like’ን ምን እንበል ስንል በቶሎ የሚመጣልን ቃል ‘ወደደ’ ነው። ግን “እባካችሁ ይህን ... ውደዱት” ማለትን ውስጣችን የሚቀበለው አይመስልም። ለዚህ አንዱ ምክንያት እንደማንኛውም አዲስ ነገር ቃሉን በአዲስ አገባብ መልመዱ ጊዜ ከመሻቱ የተነሳ ቢሆንም፣ አቢዩ ምክንያት ግን በእንግሊዝኛው በ‘like’ እና ‘love’ የሚገለጹትን ገርና ምር የፈቃደ ልቡና ስሜቶች ጠቅልሎ የያዘ የዘወትር ቃል በመሆኑና ይህን ብቸኛ ቃል ከእንግሊዝኛው አንጻር ለሌላ ሶስተኛ አገባብ ማላመዱ ፍቹን ስለሚያደበዝዘው ነው።
አማርኛ እኮ ሌላ ተመሳሳይ ስርወቃል አለው፤ እሱም ‘ሰየ’ ይባላል። ከብዙው በጥቂቱ የተለመዱት ውልድ ቃላቱ የሚከተሉት ናቸው፦ “(አ)ሻ”፣ “እሰይ”፣ “እሺ”። “ተሰየ”ን የአማርኛ መዛግብተቃላት እንደሚከተለው ይፈቱታል፦ “ጐመዠ፣ ተቃረ፣ ጓጓ፣ ቋመጠ” (ደስታ ተክለወልድ)፣ “ጎመዠ መብልንም ኾነ መጠጥን ወይም ውብ መልከ መልካም ሴትን ዐይቶ በዐሳቡ በልቡ ተመኘ ጎመጀ ሰየ” https://dictionary.abyssinica.com/። የመዛግብተ ቃላቱ አፈታት የሚያመለክተን ቢያንስ ከዛሬ ግማሽ ምእት አመት በፊት ገደማ የነበረውን የቃሉን አገልግሎት ነው። ከተለመዱት ውልድ ቃላቱ የምናገኘው ስሜት ግን ልክ እንደእንግሊዝኛው ‘like’ በገሩ የሚገለጽ ምኞትና የልቡና ፈቃድ ነው። እስቲ ገባ ብለን የውልድ ቃላቱን ስሜት እንመርምር።
“የቃላት ትንታኔና ፈጠራ” በሚል ርእስ ባቀረብኩት ቀዳሚ ጽሑፍ እንዳመለከትኩት [ሸ] በ [ይ] የቀለመ [ሰ] መሆኑን ይዘን ስንነሳ ‘አሻ’ እና ‘እሺ’ በውስጣቸው ‘ሰየ’ን መያዛቸውን ለመቀበል አያዳግተንም። አሻኝ “አሰየኝ (አሰኘኝ)፣ ፈቀድኩ ተመኘሁ”፣ እሺ ደግሞ “እሰይ፣ ፈቀድኩ፣ ይሁን አልኩ” ማለት ነው። የተመኘነው ወይም የምንፈቅደው ነገር ሲሆን የሁልጊዜ የደስታ ስሜት መግለጫችን በቀጥታ “እሰይ[አለሁ]” ነው።
እኔ ለጨዋታ በደረስኩበት ዘመን የብይ ጨዋታ በአዲስ አበባና ምናልባትም በሌሎች ትላልቅ ከተሞች የወንዶች ልጆች ተወዳጅ ጨዋታ ነበር። በዚያ ዘመን የነበራችሁ እንደምታስታውሱት በጨዋታው መሃል “ሰይ ብል/ባትል” የሚል የባለተራና የሌሎች ተፎካካሪዎች እሽቅድድም ነበር። ወደአጨዋወቱ ህግ ዝርዝር ሳንገባ፣ ባለተራ የሆነ ተጫዋች ለራሱ ብይ ይቀርባል ወይም ለመምታት ይቀናኛል ያለውን አንድ የተፎካካሪ ብይ አመልክቶ እሷኑ ብቻ ለመምታት ማለም አለበት። ነገር ግን በታላሚው ብይ አጠገብ ወይም በማስፈንጠሪያው አግጣጫ ሌሎች ብዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከብዙዎች መሃል መምታት ይቀልላልና ሌሎች ተፎካካሪዎች ሳያግዱት ቀድሞ “በኢላማዬ አግጣጫ ካሉት ብዮች የመታሁት እንደኢላማ ይቆጠርልኝ” ለማለት “ሰይ ብል” ይላል፤ “ያለምኩለት ባይሆንም የመታሁትን ብወድድ” ማለት ነው። እንግዲህ “ሰየ” “የሆነውን ነገር ፈቀደ፣ ይሁን አለ፣ ወደደ” ማለት ከሆነ “ሰይ አለ” ለእንግሊዝኛው “ላይክ” ጥሩ ምትክ ይሆናል እላለሁ። በዚሁ አንጻር ደግሞ “አይ” ማለት ነገርን ያለመውደድ፣ ያለመቀበል መግለጫ ስለሆነ ለ“ሰይታ” ተቃራኒ ወይም “ሰይታ”ን ለመሰረዝ በ”አንላይክ” ምትክ “አይ አለ” “አይታ” ይሆናል። የነዚህን ቃላት አገባብ በተግባር ለማየት በአማርኛ የመረጃ መረብ ጣቢያ (ድረጉልት) የ‘ውይይት’ አምድን ጎብኙ፤ በአስተያየትም ተሳተፉ፤ “ሰይ” ብዬ ሰድጄ አንከረባብቼ እንደሆነ ንገሩኝ። እንግዲህ ‘ላይክ/አንላይክ ማድረግ’ ይቅር፤ “ሰይታ”ና “አይታ”ንም ተላመዷቸው።