አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን! [ክፍል ሁለት]

የቃላት ትንታኔና ፈጠራ በአማርኛ

“አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን!” በሚል ርእስ ባቀረብኩት የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፍ በታቀደ ልማት ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር እውቀትን የልማት ሃይል ማድረግ፤ እውቀትን ለመቀበል፣ ለመፍጠርና ለማስፋፋት ቋንቋን ማዘመንና ማሰልጠን፤ ቋንቋን ለማዘመንና ለማሰልጠን ደግሞ ውስጣዊ ስርአቱን ከመገንዘብ ተነስቶ የእውቀትና የዘመናዊ አስተሳሰብ መግለጫ የሚሆኑ አዳዲስ ቃላትን እያበጁ የፈጠራ አቅሙን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አመልክቼ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ አዳዲስ የአማርኛ ቃላትን ወደመፍጠር የሚመራ የቃላት ፍች ትንታኔ ዘዴ በምሳሌ አሳያለሁ ባልኩት መሰረት እነሆ ይህን ተከታይ ጽሑፍ አቅርቤአለሁ።

አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን! በሚል ርእስ ባቀረብኩት የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፍ በታቀደ ልማት ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር እውቀትን የልማት ሃይል ማድረግ፤ እውቀትን ለመቀበል፣ ለመፍጠርና ለማስፋፋት ቋንቋን ማዘመንና ማሰልጠን፤ ቋንቋን ለማዘመንና ለማሰልጠን ደግሞ ውስጣዊ ስርአቱን ከመገንዘብ ተነስቶ የእውቀትና የዘመናዊ አስተሳሰብ መግለጫ የሚሆኑ አዳዲስ ቃላትን እያበጁ የፈጠራ አቅሙን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አመልክቼ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ አዳዲስ የአማርኛ ቃላትን ወደመፍጠር የሚመራ የቃላት ፍች ትንታኔ ዘዴ በምሳሌ አሳያለሁ ባልኩት መሰረት እነሆ ይህን ተከታይ ጽሑፍ አቅርቤአለሁ።

በቅድሚያ ለትንታኔው መነሻ የምናደርጋቸው ስነድምጻዊ (phonological) እና ስነምእላዳዊ (morphological) ጥቅልል ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

  1. በስርወቃላት (roots) ውስጥ አቋም ያላቸው ድምጾች ተናባቢዎች (consonants) ናቸው።
  2. የቀሩት ለተናባቢዎቹ ቀለም/ዜማ ሰጪና አቋም የለሽ ዋለል (vocalic) ድምጾች ናቸው።
  3. በፍች-ተድምጽ ትንታኔ የስርወቃላትን መሰረታዊ ፍች የሚወስኑት ቅሉ (unique) ተናባቢዎች ብቻ ናቸው።
  4. ደጋሚ ተናባቢዎችን ጨምሮ የሌሎቹ ዋለል ድምጾች ተግባር ዘረቃላትን ደጕሞና አጐላምሶ ወደ ስርወቃልነት ማሳደግ ነው።
  5. በልማዳዊው የፊደል ገበታ ከሳድስ ተራ ውጭ የሚገኙ ተናባቢዎች በሙሉ የዋለል ድምጾችን ቀለም የያዙ ናቸው። ዋለል ድምጾችን በአቋም ባናገኛቸውም እንደሚከተለው አርቅቀን ልንለያቸው እንችላለን፦
  • ሳድስ (ቀለም የለሽ) ፈልቃቂ (epenthetic) ድምጽ ነው።
  • ግእዝ (ቀለም የለሽ) አናባቢ (vowel) ድምጽ ነው።
  • ካእብ ቀለመ-ው ፈልቃቂ ድምጽ ነው።
  • ሣልስ ቀለመ-ይ ፈልቃቂ ድምጽ ነው።
  • ራብዕ ቀለመ-አ አናባቢ ድምጽ ነው።
  • ሃምስ ቀለመ-ይ አናባቢ ድምጽ ነው።
  • ሳብዕ ቀለመ-ው አናባቢ ድምጽ ነው።
  1. ከተናባቢዎች መሃል እንደ [ች፣ጅ፣ሽ፣ዥ፣ጭ፣ኝ፣ይ] ያሉ ልንቅ (palatalized) ድምጾች ላንቃዊነትን የቀለሙ የድድ ወይም የትናጋ ተናባቢዎች ናቸው። ስለዚህ ከቅሉ ተናባቢዎች አይደመሩም። አቀላለማቸውም እንደሚከተለው ነው፦
  • {ች← [ት]፣ ች← [ክ]}
  • {ጅ← [ድ]፣ ጅ← [ግ]}
  • {ሽ← [ስ]፣ ሽ← [ህ]}
  • {ዥ← [ዝ]፣ ዥ← [ግ]}
  • {ጭ← [ጥ]፣ ጭ← [ቅ]}
  • ኝ← [ን]
  • ይ← [ል]
  1. “እ” እና “ህ” ጕልህ የመሰረታዊ ፍች ልዩነት የሌላቸው ተወራራሽ የጕረሮ ድምጾች ናቸው። ስለዚህ በአንድ ድምጽነት ይወከላሉ።
  2. “ው” በአቋም ሲገኝ ቅሉ ተናባቢ ነው።
  3. “ጽ” እና “ጥ” ተወራራሽ ድምጾች ስለሆኑ በ“ጠ” ይወከላሉ።
  4. [ጵ፣ፕ፣ቭ] ጨርሶ የአማርኛ መሰረታዊ ድምጾች አይደሉም።
  5. ቅሉ ተናባቢዎች የሚከተሉት ናቸው፦ [{ህ፣እ}፣ል፣ም፣ር፣ስ፣ቅ፣ብ፣ት፣ን፣ክ፣ው፣ዝ፣ድ፣ግ፣ጥ፣ፍ]
  6. በመካነ ፍጥረት ወይም በአነባበብ በሚመሳሰሉ ቅሉ ተናባቢዎች መካከልም አልፎ አልፎ ተወራራሽነትና የመሰረታዊ ፍች መቀራረብ ይታያል።

[ህ←ክ]፣ [ል←ር]፣ [ል←ን]፣ [ም←ብ]፣ [ም←ው]፣ [ም←ን]፣ [ር←ድ]፣ [ስ←ዝ]፣ [ቅ←ክ]፣ [ቅ←ግ]፣ [ብ←ፍ]፣ [ብ←ው]፣ [ት←ጥ]፣ [ክ←ግ]፣ [ው←ግ]፣ [ይ←ው]

  1. በተናባቢዎች መጥበቅና መላላት ምክንያት ፍቻቸው አሻሚ የሚሆኑ ቃላትን ለመለየት ጠባቂ ተናባቢዎችን እንደሚከተለው እንደግማቸዋለን፦ “አጋደለ” ~ “አግጋደለ”።

በልማዳዊው የስነምእላድ አስተሳሰብ ድምጾች ፍች መወከል የሚጀምሩት ተቀናጅተው ምእላድ (morpheme/ ስርወቃል) ሲሆኑ ነው። ማለትም አንድ ስርወቃል በውስጡ የተሰደሩ ድምጾች እንጂ ፍቻዊ የሆኑ ንኡሳን አሃዶች አይኖሩትም። በሌላ አባባል፣ ድምጾች ለሚመሰርቱት ስርወቃል በተናጥልም ሆነ በቅንጅት የፍች አስተዋጽኦ አያደርጉም። እንግዲህ ስርወቃላት በያዟቸው ድምጾችና በሚወክሏቸው ፍቻዊ ስሜቶች የቱንም ያህል ቢመሳሰሉ ምስስሉ ድንገተኛ ነው እንጂ ስርአታዊ አይደለም ማለት ነው።

ይህን አስተሳሰብ በምሳሌ ለማስረዳት፦ ‘ቅ’፣ ‘ል’፣ ‘ጥ’ እና ‘ፍ’ ተቀናጅተው በቀላሉ የመተጣጠፍን፣ የመዟዟርን እና የፍጥነትን ሃሳብ የሚወክል [ቅልጥፍ] የሚል ስርወቃል ይሰራሉ። ስርወቃሉም ‘ቀለጠፈ’፣ ‘ቀልጣፋ’፣ ‘ቅልጥፍና’፣ ወዘተ. የመሳሰሉትን ቃላት ለመገንባት መሰረት ይሆናል። እነዚህን ድምጾች አንድ-ለሶስት፣ ሁለት-ለሁለት ወይም ሶስት-ለአንድ እያደራጀን ብናያቸው [ቅ-ልጥፍ]፣ [ቅል-ጥፍ] እና [ቅልጥ-ፍ] ይሆናሉ። [ልጥፍ]፣ [ቅል]፣ [ጥፍ] እና [ቅልጥ] ደግሞ በየራሳቸው ስርወቃላት የሚሆኑ ቅንጅቶች ናቸው። ሆኖም አንድ ስርወቃል በውስጡ ሌላ ስርወቃል አይዝምና እነዚህ የድምጽ ቅንጅቶች በ[ቅልጥፍ] ውስጥ ያሉ ስርወቃላት ናቸው አንልም። “ድምጾች ፍች የሚይዙት ተቀናጅተው ምእላድ ሲሆኑ ነው” በሚለው አመለካከት ግን እነዚህ ቅንጅቶች ሌላ አይነት የፍች-ተድምጽ ቅንጅት ይዘውም ቢሆን የ[ቅልጥፍ] ውስጣዊ ድርጅት አሃድ ሊሆኑ አይችሉም፤ አራቱ ድምጾች በአንድነት [ቅልጥፍ]ን እስከሚፈጥሩ ድረስ ‘ቅ’ እና ‘ል’፣ ‘ል’ እና ‘ጥ’ ወይም ‘ጥ’ እና ‘ፍ’ ፍቻዊ ቅንጅት አይኖራቸውም።

በሌላ በኩል ደግሞ በ[ቅልጥፍ]ና በንኡሳኑ ስርወቃላት መካከል መብራራት የሚሻ ረቂቅ የፍች ግንኙነት ይታያል። [ቅል]ን በሚይዙ ሌሎች ስርወቃላትና ውልድ ቃላት ሁሉ የመጥጠምዘዝ፣ የመዞርና የመልለወጥ ረቂቅ ሃሳብ አለ። (መቅላት፣መቀለስ፣ መቀልመም፣ መቀልበስ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።) እንዲሁም [ጥፍ]ን በሚይዙ ስርወቃላትና ውልድ ቃላት ሁሉ የገጾች መላተምና የመጋጠም ረቂቅ ሃሳብ አለ። (ማጠፍ፣ መለጠፍ፣ ማንጠፍ፣ መዘንጠፍ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።) ከላይ የገለጽነው የ[ቅልጥፍ] ረቂቅ ፍችም የነዚህን ንኡሳን አሃዶች ፍች ያካተተ ነው። [ቅል]፣ [ቅልጥ] እና [ቅልጥፍ] [ቅል]ን ስለሚጋሩ፣ እንዲሁም [ጥፍ]፣ [ልጥፍ] እና [ቅልጥፍ] [ጥፍ]ን ስለሚጋሩ ድንገተኛ ያልሆነ የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ አላቸው። ስለዚህ ከልማዳዊው አስተሳሰብ በተቃራኒ [ቅልጥፍ] በውስጡ ፍቻዊ አሃዶችን ይዞ ይታያል።

በተለይ ደግሞ በውስጣቸው ጥንድ ተናባቢዎችን ይዘው እነዚያኑ ተናባቢዎች በከፊል ወይም በሙሉ በመድገም ብቻ የሚለያዩ ስርወቃላት የፍች ዘራቸውን ከጥንዶቹ ተናባቢዎች እንዳገኙ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ከዚህ በታች በቀረበው ሰንጠረዥ በንኡስ ተራ (ሀ) ስር በሚገኙት ስርወቃላት እንደምናየው ደጋሚዎቹ ስርወቃላት የመሰረታዊውን ጥንድ ጽንሰሃሳብ ከማራዘም፣ ከማስፋፋትና ከማጠናከር በቀር አዲስ ጽንሰሃሳብ አይወክሉም። እንግዲህ ባለብዙ ተናባቢ ስርወቃላት አነስተኛ ፍቻዊ አሃዶችን ይዘው መገኘታቸው፣ ምእላድን የፍቻዊነት መነሻ አድርገን መቍጠራችንን እንድንተው ያስገድደናል። የፍች-ተድምጽ ቅንጅቶችንም በጥልቀት ለመመርመር ከልማድ ወጥተን ንፍቅ-ምእላዳዊ (sub-morphemic) ትንታኔ ማድረግ ያስፈልገናል ማለት ነው። በንፍቅ-ምእላዳዊ አመለካከት በባለብዙ ተናባቢ ስርወቃላት ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ፍቻዊ አሃዶችን ከስርወቃላት ለመለየት ዘረቃላት (etymons) እንላቸዋለን። ዘረቃላት ቃላትን ለመገንባት ፍቻዊና ድምጻዊ መሰረቶች ናቸው። የቃላት ግንባታው አካሄድም እንደሚከተለው ይሆናል፦

ዘረቃል (+ ደጓሚዎች) = ስርወቃል → (መልከ)አምድ       = አምደቃል (+ ምእላድ) = ሙሉ ቃል

[ቅል]     + [ስ]        = [ቅልስ]   → ደራግ-1ግእዝ22ራብእ3    = ቀላስ       + ሳልስ    = ቀላሽ 

የትንታኔው አካሄድ ደግሞ የግንባታው ሂደት የኋሊት ሆኖ፣ በቅድሚያ ከሙሉቃሉ ላይ ስነምእላዳዊ ቅጥያዎችን አራግፎ አምደቃሉን መለየት፣ ከዚያም ለስርወቃሉ የአምድ መልክ የሚሰጡትን ዋለሎችንና ደጋሚ ተናባቢዎችን ትቶ የስርወቃሉን መሰረታዊ ተናባቢዎች መለየት፣ ስርወቃሉ ደጓሚዎች (ደጋሚ ተናባቢዎች፣ ውሁዳን ዋለሎች ወይም አጎላማሽ ቅጥያዎች) ካሉት እነሱን ትቶ ቅሉ ተናባቢዎችን በሰልፋቸው መለየት። የስርወቃሉን ተናባቢዎች በጥንድ የሚጋሩና በፍችም የሚቀራረቡ በቁጥር ከአራት የማያንሱ ሌሎች ስርወቃላት ካሉ ጥንዶቹን ተናባቢዎች በዘረቃልነት መወሰንና በመጨረሻም ዘረቃሉን በሚጋሩ ስርወቃላት የፍች ተመሳሳይነት ላይ ተመርኵዞ ለዘረቃሉ ፍች ማርቀቅ ነው። በሚከተለው ሰንጠረዥ እያንዳንዱን የአማርኛ ተናባቢ በአንድ ባለጥንድ ተናባቢ ዘረቃል እየወከልን በቅድሚያ በ(ሀ) ተራ ዘረቃላቱ አዲስ ተናባቢ ሳይጨምሩ በዋለሎችና በደጋሚ ተናባቢዎች እየተደጎሙ አንድ የፍች መሰረት ያላቸው የተለያዩ ስርወቃላትን እንደሚፈጥሩ እናያለን። በስርወቃላቱ የፍች አንድነት ላይ ተመስርተን የዘረቃላቱን ፍች ካረቀቅን በኋላ በ(ለ) ተራ ደግሞ ያው ዘረቃል በሌሎች ተናባቢዎች እየተደጎመ የሚፈጥራቸው የተለያዩ ስርወቃላት መሰረታዊውን ፍች እንዴት እንደሚወርሱ እናያለን። ከዚያም በፍች-ተድምጽ ትንታኔው ሊተኮሩባቸው የሚገባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለማመልከት በጥቂት ተጨማሪ ምሳሌዎች ማብራሪያ እናክላለን።

ተራ ቍጥርዘረቃልስርወቃላት በግስ መልከአምድየጋራ ፍችየጋራ ፍች በእንግሊዝኛ

1ሀ

ልግ

 

 

ላገ፣ ለገገ፣ ለገለገ

መርዘም፣ መቅጠን፣ መልለጠጥ፣ መስሳብ፣ መቀጠል

stretch, extend

1ለ

ለገ

ለገጠ/ለጐጠ

ለጐ

ለገ/ማለገ

ለገ

ለገ

give; hand out

stick out (tongue/ mucus)

spit, throw lump

be slimy or viscous

stretch

track, trail

2ሀ

ምጥ

ማጠ፣ መጠጠ፣ መጠመጠ

የአየር/ የፈሳሽ ማለፊያ መጣበብና የግፊት/ስበት መፈጠር/መጠናከር

suction

2ለ

መጠ

መጠ

መጠ

eject

limit

sink, be sucked

3ሀ

ስል

ሳለ፣ ሰለለ፣ ሰለሰለ

መሳሳት፣ መቅለል፣ ማነስ፣ የአቅም መቀነስ

thinning, smoothing

3ለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

ሰለ

faint

grind fine

disappear

mild, soft

slither, slick

adapt

soften by cooking

4.ሀ

ርቅ

ራቀ፣ ረቀቀ፣ ረቀረቀ

ለአይን ማነስ፣ የውፍር መቀነስ፣ መሸራረፍ

fine grained

4ለ

ሰረቀ

ደረቀ

ፈረቀ

ooze

lose moisture

split

5ሀ

ቅር

ቀረ፣ ቀረረ፣ ቀረቀረ

ከመወሰድ፣ ከመቅቀነስ ተረፈ

refuse, hold out

5ለ

ቀረመ

ቀረሰ

ቀረበ

ቀረዘ

ቀረደ

ቀረጠ

glean

apportion

approach

hang to drop

tear off, slice

cut out, carve

6ሀ

ብዝ

በዛ፣ ባዘዘ፣ በዘበዘ

መዝዘርዘር፣ መመናታት፣ መትተንተን

multiplying, dividing

6ለ

ባዘተ

ባዘነ

ነበዘ

ደበዘ

thin out

be lost in thought

be unconscious

blur

7ሀ

ትል

ተላ፣ ተለለ፣ ተለተለ

ለጥቆ/ተያይዞ መሄድ፣ መከታተል

stream

7ለ

ባተለ

ከተለ

ፈተለ

be preoccupied

follow track

spin

8ሀ

ንፍ

ነፋ፣ ነፈፈ፣ ነፈነፈ

አየር/ንፋስ ገፋ/ሳበ

pump/ vacuum

8ለ

ነፈሰ

ነፈረ

ነፈጠ

blow

boil

blow nose

9ሀ

ክል

ከላ፣ ከለለ፣ ከለከለ

መልለየት፣ መከፈል

fence

9ለ

ተከለ

post

10ሀ

ውል

ዋለ፣ ዋለለ፣ ወለወለ           

መዘዋወር፣ መስፋት፣ መዝዘርጋት

wiggle, shift

10ለ

ወለቀ

ወለበ

ወለደ

slip off

flap

slip through

11ሀ

ዝል

ዛለ፣ ዘለለ፣ ዘለዘለ

ወደ ታች መሳብ/መውረድ

drop, hang

11ለ

ዘለመ

ዘለሰ

ዘለገ

pend

flop

stretch

12ሀ

ድል

ደላ፣ ደለለ፣ ደለደለ

ማሸራሸት፣ ማመቻቸት፣ እኩል ማድረግ

plain

12ለ

ደለቀ

ደለበ

ደለዘ

stomp

add layer

smudge

13ሀ

ግድ

ገሳ፣ ገሰሰ፣ ገሰገሰ

በግፊ መንሸራተት፣ መጋዝ            

move

13ለ

 

 

14ሀ

ጥፍ

ጠፋ፣ ጠፈፈ፣ ጠፈጠፈ

የገጾች መላተም፣ መለጣጠቅ

flap

14ለ

ለጠፈ

ቀጠፈ

ነጠፈ

paste

clip

flatten

15ሀ

ፍስ

ፈሳ፣ ፈሰሰ፣ ፈሰፈሰ           

 

የወላላ ይዘት (ውሃ፣ አየር፣ ጥሬ፣ ወዘተ.) ከመያዣው መውጣት፣ ማፈትለክ

leak, spill

15ለ

ለፈሰ

ነፈሰ

collapse

blow

ሠንጠረዥ፦ ከዘረቃል ወደ ሥርወቃል

 

ሁሉም የአማርኛ ቃላት ከቋንቋው የፍች-ተድምጽ ዘር ነስተው የተፈጠሩ አይደሉም። የድሃ አምዶችን መልክ ይዘው የሚቀረጹ፣ ፍቻቸው በድምጽ ከሚመስሏቸው ቃላት ያፈነገጠ ነባር ቃላት (ብዙዎቹ የአካል ክፍል ስያሜዎች ከነዚህ ይመደባሉ)፣ እንዲሁም ከዘመድም ሆነ ከባእዳን ቋንቋዎች በተውሶ እንደገቡ በአመጣጥ ታሪካቸው የሚታወቁ ብዙ ቃላት በውስጡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ የተውሶ ቃላት ስር ሰድደው ወልደውና ረብተው ሊገኙ ይችላሉ። ለነዚህኞቹ “ምስጢር” እና “ፊርማ” ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ስለዚህ ስርአተኞቹንና ዘረ ብዙዎቹን ስንተነትን እነዚህንም በጥንቃቄ ማስተዋል ይኖርብናል። 

ውሁዳን ዋለሎችን ለይቶ ስርወቃላትን ስለማግኘት፦ ከ“ስንፍና” ቅጥያዋን “ና”ን ገንጥለን አምደቃሉን “ስንፍ”ን እናገኛለን። መልከአምዱ ደጋሚም ሆነ ዋለል የማይጨምር ሁሉም ተናባቢዎቹ በሳድስ ተራ የሚገኙበት ነው። ስርወቃሉም የሶስቱ ተናባቢዎች ስድር [ስንፍ] ነው። በዚሁ አይነት “አሸናፊ”ን እንመልከት። ቅጥያዎቹን “አ”ን እና በ“ፊ” ላይ የምትታየውን የሳልስ ተራ ዋለል ጥለን አምደቃሉን “ሸናፍ”ን እናገኛለን። መልከአምዱ የግእዝና የራብእ ተራ ዋለል አናባቢዎችን የያዘ ነው። ስርወቃሉ [ሽንፍ] በዋለል [ይ] የቀለመች “ስ”ን ይዟል። እሷን ስንጥል ዘረቃሉን [ስንፍ]ን እናገኛለን። የ“ስንፍና”ም ዘረቃል ይኸው ነው። የ“መስነፍ”ን እና የ “ማሸነፍ”ን የፍች አንድነት በቀጥታ በመዝገበ ቃላት ሃተታ ባናገኘውም የ“መድከም፣ መዛል፣ ጽናት ማጣት” ሃሳብ እንደሚያገናኛቸው ማስተዋል ይቻላል። “ማሸነፍ” “ማስነፍ” ነው። እንደዚሁ “ሰፈነ”ን ከ“ሸፈነ”፣ “መጨነቅ”ን ከ“መጠንቀቅ”፣ “ተከለ”ን ከ“ቸከለ”፣ “እርጅና”ን ከ“አሮጌ” በስርወቃል ማገናኘት ይከብዳል?

ልክ እንደ “ስንፍና” ከ“ብልጽግና”ም “ና”ን ስንገነጥል “ብልጽግ” የሚል አምደቃል እናገኛለን። መልከአምዱም ልክ እንደ “ስንፍ” ደጋሚም ሆነ ዋለል የማይጨምር ሶስቱም ተናባቢዎቹ በሳድስ ተራ የሚገኙበት ነው። ይህን ቃል ለየት የሚያደርገው የስርወቃሉ የ[ብልጽግ] ፍች ተናባቢዎቹ በሌሎች ቃላት ውስጥ ካላቸው የፍች አስተዋጽኦ ተነጻጽሮ ሊገኝ አለመቻሉ ነው፤ ምክንያቱም በቀጥታ ከዘረቃላዊ ተናባቢዎች ስላልተመሰረተ ነው። ቃሉ ሃረጋዊ መሰረት አለው። ይህ አይነተኛ የቃል አመሰራረት ዘዴ አይደለም። “ባለ ጸጋ” ከሚለው ሃረግ [ብልጽግ] የሚል ስርወቃል ወጥቶ፣ በባለ ሳድስ ተራ መልከአምድ ተቀርጾ “ና” ሲቀጠልበት አዲስ ቃል ተፈጠረ። አቢይ ቃሉን “ጸጋ”ን ብቻ ይዘን ወደ ዘረቃሉ ስንወርድ (መሰረቱ አማርኛ  ከሆነ) ዘረቃሉ [ጥግ] ይሆናል። ከዚህ ዘረቃል የሚገኙ ቃላት “ጥግ”፣ “ጠገገ”፣ “ጠገረ”፣ “ጠገነ”፣ ወዘተ. እንደሚያመለክቱት የ‘ማልበስ’፣ የ‘መከለል’፣ የ‘መጠበቅ’ ስሜት ያለው ይመስላል።

ስርወቃላት ጥምር ቃላትን በማዋሃድም ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ “ደመወዝ” በግእዝ የጥምረት ስርአት ከ“ደም ወወዝ” የተፈጠረ ቃል ነው። እንደዚህ ያለውም የስርወቃል ፈጠራ አይነተኛ አይደለም። “ደም ወወዝ”ን ዛሬ “ደሞዝ” እየተባለ ብንሰማውም የፍች ጽንሱን [ድምዝ] ከሚል ስርወቃል ወይም [ድምዝ] ከሚል ዘረቃል አናገኘውም። ትንታኔው የ“ደም”ንና የ”ወዝ”ን ዘረቃላትና ሃረጋዊ ጥምረት ማገናዘብ አለበት። ባለብዙ ዘር ባለመሆኑ “ደም”ን በቀላሉ ከስርወቃል ልናገናኘው አንችልም። “ወዝ” ግን እንደ “ዋዛ”ና “ውዝዋዜ” ባሉ ቃላት እንደሚታየው ከዘረቃል [ውዝ] የወጣ ነው። በፍቹም “የንክኪን መለዘብና በቀላሉ መንቀሳቀስን” ያሳስባል።

አልፎ አልፎ ደግሞ ባልተሟላ የስርወቃል ፍለጋ ሂደት ከቃላቱ ላይ እንደ “መ” እና “ተ” ያሉ ቅጥያ ምእላዶችን ባለመግደፍ ከሚደረግ ትንታኔ ቅጥያዎቹን እንደስርወቃል ዛላ ይዘው የተገነቡ ቃላት አሉ። ለምሳሌ፦ ከ“ምርኩዝ” እና ከ“ተረከዝ” “መ” እና “ተ” ካልተነጠሉ [ረከዘ] በሚለው ስርወቃላቸው፣ “ቆንጥጦ፣ መድሮ መያዝ” (በእንግሊዝኛው anchor) በሚለው ረቂቅ ፍቻቸው ላይ የተመሰረተው የሁለቱ ቃላት አንድነት አይታይም። በነገራችን ላይ፣ የ[ክ←ግ]ን ውርርስ በማሰብ “አረገዘ”ም “ሽል ቋጠረ፣ ጽንስ ያዘ” የነዚህ ቃላት ወገን እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም።

ከ“ጤነኛ” ላይ “ኛ”ን ነጥለን ስርወቃሉን [ጥን]ን ወይም ዘረቃሉን [ጥን]ን እንደምናገኘው ከ“በሽተኛ” ላይ “ኛ”ን በመነጠል ስርወቃል አናገኝም። የ“በሽተኛ” መሰረት “በሽታ” ከአምደቃል “በሽ” እና ከቅጥያ “ታ” የተደራጀ ነው። የአምደቃሉ ጠባይ ከ“አለ” ጋር እየተቀናጁ ግስ እንደሚመሰርቱት እንደነ “ደስ”፣ “ዝም”፣ “ከፍ”፣ ወዘተ. ያለ ነው። ስርወቃሉ [ብስ] ዘረቃሉም [ብስ] ናቸው። የ “በሽታ” መነሻ “በሽ አለው” እንዲህ ፍቹ ሳይጠልቅና ሳይሰፋ ቀድሞ ቀላል ‘የሆድ መታወክ’ን የሚገልጽ ቃል ነበረ፤ ከ“(ሆድ) ባሰ”፣ “(አመለ) ቢስ”፣ “(ሆደ) ባሻ” እና ከመሳሰሉት ጋር ያወዳድሩት። በነገራችን ላይ የእንግሊዝኛው “disease”ም መሰረቱ “dis-ease” ቀላል የጤና መታወክ ነበር።

አንዳንድ ቃላት ከሌላ ሴማዊ ቋንቋ የተወረሱ ቢሆኑም ቀድሞ በአማርኛ ዘረቃላዊና ስርወቃላዊ መሰረት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ “ስልክ” ‘telephone’ን የሚሰይም፣ ‘ሽቦ’ ወይም ‘ክር’ የሚል ፍች ይዞ ከጥቂት አሰርት አመታት በፊት ከአረብኛ ቋንቋ የመጣ ቃል ነው። ነገር ግን “ስልክልክ”፣ “ሰልካካ”፣ “ሾለከ” በሚሉት ቃላት እንደሚታየው ስርወቃሉ [ሰለከ] የ ‘ሽቦ’ና ‘ክር’ን የፍች ስሜት ይዞ በአማርኛ ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉትን ቃላት የትውስት ታሪካቸውን ገልጾ ከነባር ዘረቃላቸው ጋር ማዛመድ ያስፈልጋል።

እንግዲህ የአፈንጋጭ ቃላቱን አመጣጥ ከዘረቃላዊው አመሰራረት አንጻር እንዲህ ከገለጥን ስርአታዊዎቹን ቃላት በዘር ለማገናኘት የሚያስፈልገው ከላይ በሰንጠረዡ በጥቅልሉ እንደታየው ቅሉ ተናባቢዎችን የሚጋሩ ቃላትን በፍች እያነጻጸሩ የሚስማሙትን በዘረቃልነት መያዝ ነው። የፍቺ ምርመራው ዘዴ ሳይንሳዊነት የጽንሰሃሳብ መግለጫዎቹን ከመወሰን አንጻር ፍጹም ባይሆንም የዘረቃላቱ ፍች  የብዙ ተዛማጅ ቃላትን መዝገበቃላዊ ፍች ከማነጻጸር የሚረቀቅ በመሆኑ አስተማማኝነቱ ከበቂ በላይ ነው። የአንድን ዘረቃል ፍች ለማርቀቅ ቢያንስ አምስት በስርወቃል ሃረግ የሚተሳሰሩ ቃላትን ማግኘት ያስፈልጋል።

የስርአታዊ ቃላቱን አመሰራረት ጥቂት ገባ ብለን ለማየት በዘወትር አገልግሎታቸውና አፈታታቸው የሚዛመዱ የማይመስሉ የሁለት ዘረቃላት ውሉዶችን እንመልከት። ዘረቃሎቹ [ብር] እና [ጥፍ] ናቸው። የተመረጡትም ዘረብዙ በመሆናቸው ነው። የ[ብር] ረቂቅ ፍች “ከፈተ፤ ገለጠ፤ ተላቀቀ፤ ተለያየ፤ በውስጡ አሳየ፣ አሳለፈ” ሲሆን ከውልድ ቃላቱ መሃል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ [በራ፣ በር፣ በረረ፣ በረበረ፣ በረቀ፣ በረከ፣ በረገ]።

የ “ብርሃን”ን ሃሳብ የያዙ ውልድ ቃሎች ሁሉ በተለያዩ አውደንባቦች የሚጨምሯቸውን ምስላዊነት/ ዘይቤአዊነት አካትቶ የፍች ጽንሳቸው “መግለጥ፣ መክፈት፣ ማሳየት” ነው። “ዝናቡ በራ/አባራ፣ ብራ ሆነ” ማለት “ወጣ፣ ገለጠ” ማለት ነው። “በር”ም “የተከፈተ፣ መውጫ” ማለት ነው። “መብረር”ም በ“ር” መደገም መራቅን እና ቀጣይነትን አክሎ የ“መላቀቅ”ን፣ “ተለይቶ የመሄድ”ን ረቂቅ ሃሳብ ይገልጻል። “መበርበር” “መግለጥ፣ መክፈት፣ ውስጥን ማየት” ነው፤ የድርጊቱ ጥልቀትና ቀጣይነት በዘረቃሉ መደገም የተገኘ ነው። “በረቀ” “ድንገተኛ የብርሃን መገለጥ”ን ረቂቅ ሃሳብ ይይዛል። ከዚህ ዘረቃል የሚወጡት “መብረቅና” “ብርቅ” በመጀመሪያ እይታ የሚገናኙ አይመስሉም። ግን ቀስ ብለን ብንመረምር “ብርቅ” ማለት “እንደልብ የማይገኝ፣ ውድ፣ የከበረ ዋጋ የሚሰጠው፣ ከዚህም የተነሳ ደብቀን የምንጠብቀውና ለአንድ አፍታ ብቻ ገልጠን የምናየው/የምናሳየው ነገር” ነው። ከ“መብረቅ” ጋር የሚያዛምደውም ለአንድ አፍታ ብቻ ተገልጦ መታየቱ ነው። “መብረቅረቅ”ም በደጋሚ አምደቃሉ ከሚጨምረው የእይታ ድግግሞሽ በቀር የያዘው ያው የ“ድንገተኛ ብርሃን መገለጥ”ን ሃሳብ ነው። “በረከ” እና “በረገ”ም በየውልድ ቃሎቻቸው የያዙት ረቂቅ ሃሳብ “ከግንኙነት ጽናት ማጣት፣ ድንገት መከፈል፣ መለየት” ነው። 

የ[ጥፍ] ረቂቅ ፍች “ሁለት ገጾችን/ፊቶችን አማታ፣ አገናኘ፣ ገጠመ” ማለት ሲሆን፣ ከውልድ ቃላቱ መሃል የሚከተሉት ይገኛሉ፦  [ጠፋ፣ ጣፈ፣ ጠፈፈ፣ ጠፈጠፈ፣ ነጠፈ፣ አነጠፈ፣ ተንጠፈጠፈ፣ ለጠፈ፣ አጠፈ፣ ቀጠፈ፣ ዘነጠፈ]።

“መሰወር” የሚለው የ “መጥፋት” ፍች ቀጥተኛ አይደለም፤ “ሁለት ገጾችን ማማታት” የሚያስከትለው ‘ስውር’ ፍች ነው፤ በአንዱ ወይም በሁለቱም ተጋጣሚ ገጾች ላይ ያለ ምስል ወይም ቀለም ይሰወራል። “በጥፊ መታ” የሚለው ፍች ግን በድምጽ ስሜቱም ጭምር በቀጥታ የሚመስለው ነው። “(ቀዳዳ) መጣፍ፣ መጠፍጠፍ፣ መለጠፍ” እነዚህም ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። “መንጠፍ” “ይዘትን አፍስሶ/ አውጥቶ ከመጨረስ የሚመጣ “መሰለግ፣ የውስጥ ገጽ መጣጋት” ነው። “መንጠፍጠፍ”ም በአምደቃሉ ይለይ እንጂ ያው “መንጠፍ” ነው። “መለጠፍ” እና “ማጠፍ” በፍቻቸው “የገጾችን መላተም” በቀጥታ ያሳያሉ። “መቅጠፍ” በጥቂቱ/ በአጭሩ፣ እንዲሁም “መዘንጠፍ” በስፋት/ በረጅሙ “አጥፎ መቁረጥ”ን ሲያመለክቱ “የገጾችን መጋጠም” በቀጥታ እናየዋለን።

በመጨረሻም በተከተልነው የትንተና ዘዴ “ነጋዴ”ን፣ “እንግዳ”ን፣ “ነገድ”ን እና “መንገድ”ን በ[ንግድ] ማገናኘት ፈታኝ አይሆንም። የስርወቃሉን ፍች መወሰንስ? ምናልባት የ “ነጋዴ” እና የ “ነገድ” ፍችዎች ትንሽ ይርቁብን እንደሆን እንጂ በያዝነው የፍች ምልከታ ሌሎቹን በቀላሉ ከ “መሄድ፣ መጓዝ” ጋር እናገናኘዋለን። እርግጥ ነው ቆም ብለን ካላሰብን በዘወትር እይታችን “እንግዳ”ን ከ “መንገድ” አናገናኘውም፤ በባህላችንም መንገደኛ እንግዳ ማስተናገዱ እየቀረ ስለሆነ። “ነጋዴ”ም “ነጓጅ፣ ተጓዥ፣ ወራጅ”፣ “ነገድ”ም “የትውልዶች ተዋርድ፣ የክትትል ጉዞ” ናቸው። የስርወቃሉም ፍች ሲጠቃለል “ተከታትሎ መሄድ፣ መውረድ” ይሆናል። እንግሊዝኛውም ይህን መሰረታዊ ፍች በአንድ ዘረቃል ይወክላል በ[tr]: tribe, trade, track, trip, travel, train, trend, … የቃላት ፍች ምርመራ አቅማችንን ለማነቃቃት እስካሁን ያየነው ይበቃል።

እንደዚህ በብዙ ስርወቃላት ውስጥ የሚገኙ ባለሁለት ተናባቢ ዘረቃላትን እየለየን ፍቺዎቻቸውን ካረቀቅን፣ ደግሞ ከዚያ ዘልቀን እያንዳንዱ ተናባቢ በየዘረቃሎቹ የሚያበረክተውን የፍች አስተዋጽኦ የዘረቃላቱን ፍች በማወዳደር አንጥረን ማውጣት እንችላለን። በዚህ አይነት የአስራ ስድስቱም የአማርኛ ቅሉ ተናባቢዎች ረቂቅ ፍች ይወሰናል። በያንዳንዱ ቃላት ውስጥ በስርወቃላቱ በኩል የፍች መሰረት ሆነው የሚገነቡት እነዚህ የተናባቢዎቹ ረቂቅ ፍችዎች ናቸው። እንዲህ ነባር ቃላትን በያዟቸው ድምጾች አይነትና ሰልፍ እያነጻጸርን የፍች ዝምድናቸውን መመልከት ከቻልን አዳዲስ ውልድ ቃላትን በቅድሚያ ከስርወቃላት ሲያልፍም ከዘረቃላት ለመፍጠር ጽኑ መሰረት አገኘን ማለት ነው። አዳዲስ ቃላትን ለማግኘት ነባሮቹንና የአፈጣጠር ስርአታቸውን ጠለቅ ብሎ መመልከት እንጂ ከሌሎች ቋንቋዎች ለማምጣት አሻግሮ መመልከት አያስፈልግም።

ከመሰናበቴ በፊት በቀዳሚው ጽሑፌ እንዳመለከትኩት በጥቂቱ ለማሳየት የሞከርኩትን የፍች ምርመራና የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በሰፊው አሳውቄ ታታሪ የሆኑ ግለሰቦችን በማስተባበር የአማርኛን ልማት ለመምራት ተነስቻለሁ። ለዚህም ስለአማርኛ ቋንቋ ልማት ሃሳብ ለመለዋወጥ የሚያግዝና በቀጥታ ቃላትን በመፍጠር፣ በማከማቸትና በማሰራጨት ተግባዊ እንቅስቃሴው የሚከናወንበት በhttp://amharic-language.com አድራሻ የሚገኝ ድረገጽ በቅርቡ እከፍታለሁ። ድረገጹን እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ። አስተያየቶቻችሁን በ btadata@gmail.com ብትልኩልኝ በደስታ እቀበላለሁ።

ኑ! አማርኛን እናሰልጥን!

በዛ ተስፋው አያሌው